
ባሕር ዳር፡ መስከረም 27/2013ዓ.ም (አብመድ) የአማራ ኢኮኖሚ ሽግግር ማዕከል ለክልሉ የኢኮኖሚ ዕድገት በትኩረት እንደሚሠራ አስታውቋል፡፡
ከአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት ጋር ቆይታ ያደረጉት የአማራ ኢኮኖሚ ሽግግር ማዕከል ፕሬዝዳንት ለጤናህ እጅጉ (ዶክተር) ማዕከሉ የአማራ ኢኮኖሚ ወደ ላቀደ ደረጃ እንዲሸጋገር የሚሠራ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ የኢኮኖሚ ሽግግር ሲባልም አሁን ካለበት የኢኮኖሚ መዋቅር ወደ ተሻለና ዘመናዊ ኢኮኖሚ መዋቅር ማሻገር እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡ “ኢኮኖሚ ተሻገረ የሚባለው ከመጀመሪያ ደረጃ ወደ ሁለተኛና ከፍተኛ ደረጃ ኢኮኖሚ ሲሸጋገር ነው” ያሉት ዶክተር ለጤናህ “የአማራም ሆነ አጠቃላይ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ግብርና ተኮር ነው፤ ግብርናውን በማሳደግ ወደ ኢንዱስትሪ ተኮር ማሻገር ይገባል” ነው ያሉት፡፡ ግብርና ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋፅዖ እንዳለውና ግብርናውን ማዘመን ላይ መሠራት ያለበት መሆኑንም አመላክተዋል፡፡
ማዕከሉ ክልሉን ሊያሳድግ ሲነሳ ግብርናውን ማሳደግና ተጨባጭ የሆነ ለውጥ እንዲመጣ የማድረግ ሥራ እንደሚሠራም ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል፡፡ ከሁሉም አስቀድሞ በቂ ሰብል ማምረትና በበቂ ሁኔታ መመገብ ላይ እንደሚሠራና ከዚያ ሲያልፍ ወደ ቀጣዩ ሥራ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ እንደ ዶክተር ለጤናህ ማብራሪያ የግብርና ትራንስፎርሜሽኑ ከወረቀት ባለፈ በተግባር መታየት መቻል አለበት፤ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ጎን ለጎን ኢንዱስትሪውን ማምጣት ይገባል፤ አብዛኛዎቹ የኢንዱስትሪ ፓርኮች በቂ የግብርና ምርት የላቸውም፤ እናም ባለሀብቶች በኢንዱስትሪው ዘርፍ ለመሰማራት ቢፈልጉም በቂ የግብርና ምርት ስለማይገኝ ሐሳባቸውን ሳያሳኩ ይቀራል፡፡
የአማራ ኢኮኖሚ ሽግግር ማዕከል ‘‘ኢኮኖሚው ይሻገር’’ ሲል ግብርናውን መርሳት ሳይሆን ግብርናውን አዘምኖ ወደ ኢንዱስትሪ ማደግን ዓላማ ያደረገ እንደሆነ ፕሬዝዳንቱ አስታውቀዋል፡፡ ማዕከሉ ለትርፍ የተቋቋመ አለመሆኑን የተናገሩት ዶክተር ለጤናህ እጅጉ ‘‘ኢኮኖሚውን ለማሳደግ ጥናቶችን በማቅረብ፣ ፕሮጀክት በመቅረፅ፣ በመተግበርና በማማከር ሐሳቦችን መንግሥትና ሕዝብ እንዲገዛቸው የማድረግ ሥራዎችን ይሠራል’’ ብለዋል፡፡ በማዕከሉ የሚመነጨው ሐሳብ ተግባራዊ እንዲሆን እንደሚሠራም ገልጸዋል፡፡ ለአብነትም በግብርናው ዘርፍ የሚስተዋሉ ችግሮችን በማጥናት ችግሮቹን ለይቶ መቀመጥ ሳይሆን የሚያስፈልገውን የመፍትሔ ሐሳብ መተግበር ላይ እንደሚሠራ ጠቁመዋል፡፡ ማዕከሉ እስካሁን ድረስ ተቋሙን ሕጋዊ የማድረግ ሥራ፣ አባላትን የመመዝገብ፣ ቢሮዎችን የመክፈትና የድርጅቱን መዋቅር የመሥራት ሥራ ሲሰራ እንደቆዬ ፕሬዝዳንቱ ጠቅሰዋል፡፡ ማዕከሉ የጥረት ኮርፖሬትን አጠቃላይ ሂደትና በሥሩ ያሉ ኩባንያዎችን ለመጎብኘት በሂደት ላይ መሆኑን የተናገሩት ዶክተር ለጤናህ ኮርፖሬቱ ያለበትን ችግር በሳይንሳዊ ዘዴ ለመፍታት እንደሚሠሩም አስታውቀዋል፡፡
ማዕከሉ ቀደም ሲል ከተመሠረተው የአማራ ምሁራን መማክርት ጉባኤ ጋር የመደራረብ ሂደት እንዳይፈጠር ውይይት ማድረጉንና ዓላማው የአማራን ኢኮኖሚ መደገፍ እንጂ ተደጋጋሚ የሆነ ተቋም ፈጥሮ መቀመጥ አለመሆኑንም ዶክተር ለጤናህ አስረድተዋል፡፡ የአማራ ምሁራን መማክርትን ጨምሮ ሌሎች በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች የማይደርሱበትንና ያላዩትን መሥራት እንጂ እነርሱ የሠሩትን የመድገም ሥራ እንደማይሠሩም ገልጸዋል፡፡ ከአማራ ምሁራን መማክርት ጉባኤ ጋርም በጋራ እንደሚሠራ ነው የተናገሩት፡፡ ማዕከሉ መንግሥት “ይሄን ይሥራ” ሌላው አካልም “ይሄን ይሥራ” ብሎ የሚቆም ሳይሆን ሠርቶ የሚያሳይ መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡ ይህ ካልሆነ ሥሩ በማለት ብቻ የኢኮኖሚ ሽግግር ሊመጣ እንደማይችልም አስረድተዋል፡፡
የአማራ ኢኮኖሚ ሽግግር ማዕከል ለክልሉ ተጨባጭ የሆነ የኢኮኖሚ ለውጥ ለማምጣት የሚሠራ መሆኑንም አስምረውበታል፡፡
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m