
ባሕር ዳር፡ መስከረም 27/2013ዓ.ም (አብመድ) በአዲስ አበባ የአማራ ባህል ማዕከልን ለመገንባት የቦታ ጥያቄ ማቅረቡን የአማራ ልማት ማኅበር (አልማ) ገለጸ፡፡ የማኅበረሰቡ ተሳትፎ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም አልማ ጥሪ አቅርቧል፡፡
ማኅበሩ በሦስት ዓመታት ስትራቴጂካያዊ እቅዱ ሊሠራ ካሰባቸው ማኅበራዊ ልማቶች መካከል በአዲስ አበባ የሚገነባው የአማራ ባህል ማዕከል አንዱ ነው፡፡ የባህል ማዕከሉ የአማራ ሕዝብ ቱባ ባህል፣ ወግ እና እሴት ተጠብቆ እንዲቆይ ለማድረግ ታስቦ የሚሠራ ነው፡፡ በአዲስ አበባ እና ከክልሉ ውጪ ያሉ የብሔሩ ተወላጆችም ባህላቸውን ጠንቅቀው እንዲያውቁ ዕድል ይፈጥራል፡፡
ማዕከሉ ታሪክን እና የቱሪዝም መዳረሻዎችን ለሌሎች ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በማስተዋወቅም ማኅበራዊ ትሥሥርን ያጠናክራል፡፡ የአማራ ሕዝብን ትክክለኛ ማንነት አጉልቶ በማሳየት እና የተሳሳተ ትርክትን በማስወገድም የጋራ ሀገር የመገንባት ፖለቲካዊ ፋይዳ ይኖረዋል፡፡ ወደ አማራ ክልል ማቅናት የማይችል ጎብኝ ባህላዊ እና ቁሳዊ ቅርሶችን እንዲያውቅ ያደርገዋል፡፡ በክልሉ ሊጎበኙ የሚገባቸውን መረጃ በመስጠትም የጉብኝት እቅድ እንዲይዙ ያነሳሳል፡፡
በአማራ ልማት ማኅበር (አልማ) የአዲስ አበባ እና ሌሎች ክልሎች ማስተባበሪያ ዳይሬክተር ደጋረገ ስዩም እንደገለጹት ባህል ማዕከሉ መዝናኛ፣ የውይይት መድረኮች፣ የምርምር ሥራዎች የሚከናወኑበት እንዲሆን ታስቧል፡፡ ይህም ገቢውን በማሳደግ ማኅበሩ ራሱን ከማስተዳደር አልፎ ለሌሎች የክልሉ ማኅበራዊ ልማቶች የበጀት ምንጭ ያደርገዋል፡፡ የከተማውን ውበት በመጠበቅ፣ በሥራ እድል ፈጠራ፣ የግብር የገቢ ምንጭ በመሆንም ጉልህ ሚና ይኖረዋል፡፡
የባህል ማዕከሉ ግንባታ ተግባራዊ እንቅስቃሴ የተጀመረው ታኅሣስ 15/2012 ዓ.ም ነው፡፡ ግንባታው እንዲሆን የታሰበው ለጉብኝት ቀላል፣ ከፍተኛ የሕዝብ ፍሰት እና የትራንስፖርት አገልግሎት ባለበት ማዕከላዊ ቦታ ነው፡፡ ለምርምር ማዕከላት እና ለዩኒቨርሲቲዎች ቅርብ እንዲሆንም ይፈለጋል፡፡
ዳይሬክተሩ እንዳሉት እንቅስቃሴው ከተጀመረ አንስቶ ቦታ ለማግኘት ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ የ50 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ጥያቄም በክልሉ መንግሥት በኩል ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቀርቧል፡፡ ከከተማ አስተዳደሩ ጥሩ ተስፋ ቢኖርም የመሪዎች መለዋወጥ በእንቅስቃሴው ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩን አቶ ደጋረገ አመላክተዋል፡፡
ቦታው እንደተገኘ የሚከለስ ቢሆንም የማዕከሉ ዲዛይን ምን መምሰል እንዳለበት በበጎ ፈቃደኛ ባለሀብቶች፣ በምሁራን እና በሌሎች አስተያየት እየዳበረ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ቦታው ሲገኝ ቶሎ ሥራ ለመጀመርም ገንዘብ የማሰባሰብ እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡ ምንም እንኳን ውጫዊ ችግሮች ቢገጥሙም የነበረው እንቅስቃሴ አበረታች መሆኑን አንስተዋል፡፡ የኮሮናቫይረስ ከመከሰቱ በፊት በ45 ቀናት 63 ሚሊዮን ብር ገደማ ተሰብስቧል፡፡ እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ እና መንግሥታዊ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራሞች መደራረብ እንቅሰቃሴውን በሚፈለገው ልክ እንዳይሆን አድርጎታል፡፡ በተያዘው ዓመትም ገቢ የማሰባሰብ ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል፡፡
“ማኅበሩ የባህል ማዕከሉን የሚገነባው ከመላው የአማራ ተወላጅ እና የልማት ደጋፊዎች በሚሰበሰብ ገንዘብ ነው” ያሉት አቶ ደጋረገ ጅምሩ ከግብ እንዲደርስ ማኅበረሰቡ ርብርብ እንዲያደረግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m