
ባሕር ዳር፡ መስከረም 26/2.13ዓ.ም (አብመድ) አዲሱ የኢትዮጵያ የብር ኖት በሰሜን ገንደር ዞን ጠለምት ወረዳ አገልግሎት እየሰጠ አለመሆኑን የወረዳው የመንግሥት ሠራተኞች ለአብመድ ተናግረዋል፡፡
በሰሜን ጎንደር ዞን የሚገኜው የጠለምት ወረዳ የባንክ አገልግሎት አያገኝም፡፡ ይህ ወረዳ የባንክ አገልግሎት ባለማግኜቱ ለከፍተኛ ችግር እየተጋለጠ መሆኑን ነዋሪዎቹ በተዳጋጋሚ ይናገራሉ፡፡ ኢትዮጵያ አዲስ የብር ኖቶችን ይፋ ባደረግችበት ወቅት ያነጋገርናቸው የጠለምት ወረዳ ነዋሪዎች የባንክ አገልግሎት ባለመኖሩ ኖቱን ለመቀዬር አስቸጋሪ መሆኑን መናገራቸውን ዘግበን ነበር፡፡ አሁን ላይ የብር ኖቱ ቅዬራ እንቅስቃሴ ምን ይመስላል ስንል ዳግም ዘገባ ሠርተናል፡፡
የጠለምት ወረዳ የግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ዮሐንስ ሞላ “በወረዳው አዲሱ የብር ኖት በገበያ ልውውጥ ላይ አይታይም” ብለዋል፡፡ እርሳቸውም ብሩን እስካሁን አይተውት እንደማያውቁ ነው የተናገሩት፡፡ የባንክ አለመርም በማኅበረሰቡ ላይ ተፅዕኖው ከፍ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
“አርሶ አደሩ ከጎረቤት ወረዳዎች እየሄደ ብር ሊቀይር ይችላል፤ ነገር ግን አመቺ አይደለም” ነው ያሉት፡፡ በወረዳው ከአማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም (አብቁተ) ውጭ ሌላ አማራጭ እንደሌለ የተናገሩት ዮሐንስ አዲሱ ብር ሊመጣ የሚችለው ለመንግሥት ሠራተኛው የደመወዝ ክፍያ ሲፈፀም ሊሆን እንደሚችልም ግምታቸውን አስቀምጠዋል፡፡ አርሶ አደሩ በአብቁተም ሆነ በሌሎች አማራጮች ብሩን እንዲቀይር የግንዛቤ ፈጠራ መሥራት እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡ በወረዳው የብር ኖት ቅዬራ ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ ያለውን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ለማነቃቃት ባንክ እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል፡፡
ሌላኛው ሐሳብ የሰጡን አቶ ኃይለማርያም ብርሃኔ “በተጠቃሚዎች የብር ልውውጥ ላይ አዲሱ የብር ኖት የለም” ብለዋል፡፡
የጠለምት ወረዳ አስተዳደሪ መርሻ ወረታ የባንክ አገልግሎት ባለመኖሩ የብር ለውጥ ሲደረግ ችግር እንደሚያጋጥም ታሳቢ ተደርጎ ስለነበር በአብቁተ በኩል መፍትሔ መቀመጡን ገልጸዋል፡፡ “ማኅበረሰቡ በአብቁተ አማካኝነት ብሩን እንዲቀይር ግንዛቤ ፈጠራ ተፈጥሯል” ብለዋል፡፡ ነገር ግን ብር ቀይሮ ለመሄድ በቅርብ ያሉ ባንኮችና አብቁተ አዲሱ የብር ኖት በበቂ እንደሌላቸው ገልዋል፡፡
ማኅበረሰቡ በቤቱ ያለውን ገንዘብ አምጥቶ አዲስ የሒሳብ ቁጥር በመክፈት ወይም ባለው ላይ ማስገባት እንደሚችልም ተናግረዋል፡፡ “በርከት ያለ ብር ይዞ የሚንቀሳቀስ በሕገ ወጥነት ይፈረጃል የሚለው ጉዳት እንዳያደርስና በወረዳው ያሉ ነጋዴዎች እንግልት እንዳይደርስባቸው ኬላ ላይ ላሉ ባለሙያዎች ግንዛቤ በመስጠት ሕጋዊነታቸውን እያረጋገጥን እንዳይንገላቱ ለማድረግ ተሞክሯል” ነው ያሉት፡፡ በወረዳው የገበያ ልውውጡ በአዲሱ የብር ኖት አለመሆኑ አሮጌው የብር ኖት ለረጅም ጊዜ ይዘልቃል የሚል ስጋት መኖሩንም ተናግረዋል፡፡
በወረዳው የእንስሳት ሽያጭ የሚያካሂዱ፣ በማኅበር ገንዘብ የሚሰበስቡ፣ የሃይማኖት ተቋማትና ሌሎች ገንዘብ በእጃቸው ሊኖራቸው የሚችሉ አካላትን መቶ ሺህ እና ከዚያ በላይ የሆነ ብር የመቀዬሪያ ቀን ከማለፉ አስቀድመው እንዲቀይሩ የማድረግ ሥራ እየተሠራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
በወረዳው የተጭበረበረ የብር ኖት እንዳይኖርም እየተሠራ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡ “በአጠቃላይ ግን በወረዳው የባንክ አገልግሎት አለመኖር ከባድ ተፅዕኖ እያሳደረ ነው” ብለዋል፡፡ በወረዳው የባንክ አገልግሎት እንዲሰጥ ካመለከቱ እንደቆዩ የተናገሩት ዋና አስተዳደሪው እስከዛሬ ተግባራዊ ምላሽ አለመሰጠቱን ጠቁመዋል፡፡ የወረዳው የመንግሥት ሠራተኛ ደመወዝ አሁን ድረስ በቀደመው አካሄድ በእጅ እንደሚከፈል የተናገሩት ዋና አስተዳዳሪው “ችግሩ እንዲፈታ በተዳጋጋሚ ተጠይቋል” ነው ያሉት፡፡ በወረዳው የባንክ አገልግሎት ባለመኖሩ የሚወጣው ወጪ ሌሎች ተቋማትን ማስገንባት የሚያስችል እንደሆነም ተናግረዋል፡፡ ባንክ ለማስጀመር የመንገድ አገልግሎትና የሕንጻ አለመኖር እንደችግር እንደሚነሳም ተናግረዋል፡፡
በወረዳው በኩል “የሕንጻውን ጉዳይ በወረዳው የሚገኙ ነጋዴዎች በጋራ ሆነው ዘመናዊ ሕንጻ መገንባት እንዲችሉ የማስተባበር ሥራ ተሠርቷል፤ ካለበለዚያም ለባንክ አገልግሎት የሚመጥኑ የወረዳውን ቢሮዎች በመቀዬር ለማስጀመር የሚያስችል ሥራ እንስቃሴ እየተደረገ ነው”ሲሉም ተናግረዋል፡፡
“መስከረም 2013ዓ.ም ባንክ የሚጀምርበትን ሁኔታ ለማመቻቸት መጥተን እናያለን ተብሎ ነበር፤ ነገር ግኖ እስካሁን የታዬ ነገር የለም” ብለዋል፡፡ የክልሉ መንግሥትም የመብራት አቅርቦት በማመቻቸት እገዛ እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡ የባንክ አገልግሎቱ ጥያቄ በአስቸኳይ መፈታት ያለበት ጉዳይ መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡
ዘጋቢ፡-ታርቆ ክንዴ