ኢዜማ መንግሥት በፖሊሲ የአማራጭ ሐሳቦች ላይ ውሳኔ እና ተግባራዊ እርምጃ ከመውሰድ መቆጠብ እንዳለበት አሳሰበ፡፡

368
ባሕር ዳር፡ መስከረም 26/2013ዓ.ም (አብመድ) ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ የሕዝብን ይሁንታ ለማግኘት የተለያየ የፖሊሲ አማራጭ ሐሳቦችን ይዘው ይቀርባሉ፡፡ መንግሥት በተራዘመ የምርጫ ወቅት ላይ በእነዚህ አማራጭ ሐሳቦች ላይ ተግባራዊ እርምጃ እና ውሳኔ ከማሳረፍ እንዲቆጠብ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) አሳስቧል፡፡
ወቅታዊ በሆነው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት እንዲራዘም ሰኔ 3 ቀን 2012 ዓ.ም በሕዝብ እንደራሴዎች የተወሰነበት ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ እንዲካሄድ በቅርቡ ተወስኗል፡፡ በውሳኔው መሠረትም በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተመዘገቡ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቅድመ ዝግጅት ላይ ናቸው፡፡
ከፖሊሲ ሐሳብ ይልቅ ዘውጌነት ይጫነዋል ተብሎ የሚሰጋው ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ የስበት ማዕከሉ በአንድ አካባቢ ብቻ ይሆናል ተብሎም አይታሰብም፡፡
በበርካቶች ዘንድ በተለይም በቅድመ ምርጫ ሂደቱ አይረሴ የነበረው የ1997 ዓ.ም ምርጫ የስበት ማዕከል ከተሞች በተለይም አዲስ አበባ ነበረች፡፡ በስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ይህ ታሪክ የሚደገም አይመስልም፡፡ በየክልሎቹ ያሉት ፉክክሮች ምርጫውን በሀገር አቀፍ ደረጃ ከመጠበቅ ይልቅ የየአካባቢው ፉክክር ቀልብን እንዳይስብ የሚያሰጋ እንደሆነ የሚገምቱ በርካቶች ናቸው፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የፓርቲያቸውን ቅድመ ዝግጅት አስመልክቶ ከአብመድ ጋር የስልክ ቆይታ የነበራቸው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ ፓርቲ (ኢዜማ) የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ናትናኤል ፈለቀ መንግሥት በፓርቲዎች የፖሊሲ አማራጭ ሐሳቦች ላይ ውሳኔ እና ተግባራዊ እርምጃ ከመውሰድ መቆጠብ እንዳለበት አስታውቀዋል፡፡ እንደ አቶ ናትናኤል አስተያዬት በስልጣን ላይ ያለ መንግሥት ምርጫ በተቃረበበት ወቅት ሥራው የሕዝብን ደኅንነትና የሀገርን ሉዓላዊነት ማስጠበቅ እና ምርጫው ነፃ፣ ዴሞክራሲያዊና ፍትሐዊ እንዲሆን ማመቻቸት መሆን አለበት፤ ተመረጠም አልተመረጠ የዜጎችን ደኅንነት እና የሀገርን ሉዓላዊነት ማስጠበቅ ውድድር የሌለበት የመንግሥት የዕለት ከዕለት ግዴታ ነው፡፡ ምርጫ በተቃረበበት ወቅት በስልጣን ላይ ያለው መንግሥት ያለበቂ ጊዜ እና ዝግጅት በሚወስናቸው ውሳኔዎች ከምርጫ በኋላ ወደ ስልጣን የሚመጡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ ኋላ ለመመለስ ግድ እንደሚላቸው አስገንዝበዋል፡፡
የፖሊሲ አማራጭ ሐሳቦች የሕዝብን ቅቡልነት ማግኘት ያለባቸው ጉዳዮች መሆናቸውን አቶ ናትናኤል ገልጸዋል፡፡ የተለያዩ ፓርቲዎች የተለያየ የፖሊሲ አማራጮችን ይዘው ለውድድር ስለሚቀርቡ መሰል ጉዳዮች በይደር ሊቆዩ ይገባል ባይ ናቸው፡፡ ለአብነትም የኢትዮ-ቴሌኮምን ከፊል ድርሻ ወደ ለግል ባለሀብቶች መሸጥ ኢዜማ ተገቢ እንዳይልሆነ እንደሚያምን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው ተናግረዋል፡፡ ከምርጫ በኋላ ወደ ስልጣን የሚመጣ ፓርቲን ከፍላጎቱ እና ከአማራጭ ሐሳቡ ውጭ ለመተግበር እንደሚያስገድደውም ገልጸዋል፡፡ እንዲህ ዓይነት የምርጫ ዋዜማ ውሳኔዎች ፓርቲዎችን አጣብቂኝ ውስጥ የሚከትቱ ተግባራዊ እርምጃዎች መሆናቸውንም የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው ጠቁመዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleየኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ የሚጀመርበት ቀን ታወቀ፡፡
Next articleአዲሱ የብር ኖት በጠለመት ወረዳ አገልግሎት እየሰጠ አይደለም፡፡