በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ትምህርት ለማሥጀመር መምህራን የክፍል ድልድል እየሠሩ ነው።

167
ባሕር ዳር፡ መስከረም 26/2013ዓ.ም (አብመድ) ቅድመ መከላከል ስልቶችን ተግባራዊ በማድረግ ትምህርት ለማስጀመር ቅድመ ዝግጅት ማጠናቀቁን የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ አስታውቋል፡፡
በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ተቋርጦ የነበረውን ትምህርት ለማስጀመር በተሰጠው አቅጣጫ መሠረት ትምህርት ቤቶች የቅድመ መከላከል ተግባራትን በማከናወን የተማሪዎች ምዝገባ አከናውነዋል፡፡ ትምህርት ለማስጀመር ማሟላት የሚገባቸውን የቅድመ መከላከል መስፈርት ለማሟላት እየሠሩ ነው፡፡
አብመድ በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ውስጥ ከሚገኙ ትምህርት ቤቶች በአንዱ ተገኝቶ የቁልቋል ሜዳ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤትን የቅድመ ዝግጅት ሁኔታ ተመልክቷል፡፡ የቁልቋል ሜዳ የመጀመሪያ ደረጃ ሙሉ ሳይክል ትምህርት ቤት መምህራን ከምዝገባ በኋላ ተማሪዎችን ለመቀበል የኮሮናቫይረስ ቅድመ መከላከል የሚረዱ ሥራዎችን እየሠሩ ነው፡፡ በሦስት ፈረቃ ትምህርት ለመስጠትም የክፍል ድልድል እየሠሩ ነው፡፡
መምህርት ትርንጎ አበራ እንደነገሩን በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ተቋርጦ የነበረውን ትምህርት ለማስቀጠል መምህራን በየትምህርት ክፍላቸው የክፍለ ጊዜ ድልድል እየሠሩ ነው፡፡ በድልድሉ መሠረት ደግሞ በሦስት ፈረቃ ትምህርት ለማስጀመር በቂ ዝግጅት ማድረጋቸውን ገልጸዋል። ሰባተኛ እና ስምንተኛ ክፍል ተማሪዎችን በመጀመሪያ ፈረቃ፣ አምስተኛ እና ስድስተኛ ክፍል በሁለተኛ ፈረቃ እና ህፃናትን በሦስተኛ ፈረቃ ለማስተማር እየተዘጋጁ እንደሆነም ነግረውናል፡፡
የትምህርት ቤቱ ርእሰ መምህር አባይነህ የሺዋስ ትምህርት ለማስጀመር የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን ተናግረዋል። ግቢውን ማጽዳት፣ መማሪያ ወንበሮችን ማዘጋጀት እና የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል የሚያስችሉ ግብዓቶችን የማሟላት ሥራ እየተሠራ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ትምህርት ሲጀመር ሁሉም ተማሪ እና መምህር የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል መልበስ ግድ አንደሚሆን አስታውቀዋል፡፡ በ12 የመማሪያ ክፍሎች 1 ሺህ 217 መደበኛ እና 200 ቅድመ መደበኛ ተማሪዎችን ለማስተማር የክፍለ ጊዜ ድልድል እየተሠራ እንደሆነ ርእሰ መምህሩ አብራርተዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ኃላፊ ተሻገር አዳሙ እንደነገሩን በከተማ አስተዳደሩ በመንግሥት 11 ሁለተኛ ደረጃ እና 41 አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ይገኛሉ፤ በግል 10 ሁለተኛ እና 36 አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አሉ። በመንግሥት እና በግል ትምህርት ቤቶች ወረርሽኙን በመከላከል ትምህርት ለማስጀመር ቅድመ ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውን ኃላፊው አስታውቀዋል፡፡
የመንግሥት ትምህርት ቤቶች በሦስት ፈረቃ፣ የግል ትምህርት ቤቶች ደግሞ በሁለት ፈረቃ ትምህርት የማስተማር ሥራ እንደሚያከናውኑም ነግረውናል። በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር 122 ሺህ 160 ተማሪዎች ትምህርታቸው እንደሚከታተሉም ኃላፊው ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ:- አዳሙ ሺባባው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleየ12ኛ ክፍል ፈተናን በኦላይን ለመፈተን የሚያደርገውን ዝግጅት እያጠናቀቀ መሆኑን የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
Next articleየገበታ ለሀገር ፕሮጀክትን አስመልክቶ ለውጭ ሀገር አልሚዎች ገለፃ እየተደረገላቸው ነው፡፡