
ስለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከ47 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን የፈረሙበት ደብዳቤ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ገብቷል፡
ባሕር ዳር፡ መስከረም 26/2013ዓ.ም (አብመድ) የአማራ ኢኮኖሚ ሽግግር ማዕከል ኢትዮጵያ በዓባይ ግድብ ያላትን አቋምና ፍትሐዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ የሕዝብ ፊርማ የተሰባሰበበት ደብዳቤ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስገብቷል።
ደብዳቤው 47 ሺህ 57 ኢትዮጵያውያን ፊርማ ያረፈበት በ1 ሺህ 177 ገፅ ነው የቀረበው። ለየተመድ ሰለተላከው ደብዳቤና ስለግድቡ ያለውን ተሳትፎ በተመለከተ የአማራ ኢኮኖሚ ሽግግር ማዕከል ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል። መግለጫውን የሰጡት የማዕከሉ ፕሬዚዳንት ለጤናህ እጅጉ (ዶክተር)፣ የማዕከሉ ምክትል ፕሬዝዳንት አየለ አናውጤ እና የማዕከሉ የፓርትነርሽፕ ዳይሬክተር በላይነህ ጌታቸው ናቸው።
የሽግግር ማዕከሉ የኢኮኖሚ መዋቅሩን ወደተሻለና ዘመናዊ ኢኮኖሚ መቀዬርን ዓላማ አድርጎ የሚሠራ ነው ተብሏል። ይህ ማዕከል በበላይ ሆኖ በማስተባበር በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ላይ በመላው ዓለም የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ወዳጆች ፊርማቸውን እንዲያስቀምጡ አድርጓል። ፊርማው የኢትዮጵያውያን አቋም በግድቡ ላይ ምን እንደሚመስል የሚያሳይ ሆኖ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ገብቷል ነው የተባለው።
ማኅበሩ በጥናትና ምርምር ላይ ተመሥርቶ መንግሥትንና ሕዝብን በማሳመን በማነሳሳት የአማራን ሕዝብ ከድህነት የሚያወጣ የኢኮኖሚ ሽግግር ማምጣትን ዓለማው ያደረገ ነው። ወደ ተቋማዊ ቅርፅ ተቀይሮ ወደሥራ የገባው ማኅበሩ በታላቁ ሕዳሴ ግደብ ላይ ያለውን አስተዋፅኦ ለማሳየት ነው ፊርማ አሰባስቦ ለየተመድ ያስገባው።
ሕዳሴ ግደቡ በአፍሪካ በአንደኝነት የሚጠቀስና በዓለምም ግዙፍ ከሆኑ ግድቦች ተርታ የሚመደብ መሆኑ በመግለጫው ተነስቷል። ይህ ግድብም ለኢትዮጵያ እና ለተፋሰሱ ሀገራት ከፍተኛ ጥቅም ይኖረዋል ተብሎም ይጠበቃል። ታላቁ የሕዳሴ ግድብን ኢትዮጵያውያን በገንዘብ፣ በምህንድስናና በዲፕሎማሲ ሥራ ከፍተኛ ርብርብ ያደረጉበት መሆኑም በመግለጫው ተነስቷል። ግድቡ 65 ሚሊዮን ዜጎችን ከጨለማ ያወጣል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት መሆኑም ተመላክቷል።
ግድቡ የኢትዮጵያን አጠቃላይ ኢኮኖሚ አምስት በመቶ ወጭ እንደሚጠይቅም ነው የተነገረው። ግደቡ ሲጠናቀቅ ከኤሌክትሪክ አቅርቦት ባለፈ የዓሳ ምርት፣ ለአዳዲስ ከተሞች ግንባታና ለቱሪዝም ዘርፍም ከፍተኛ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ነው የተባለው። ግድቡ በቀጣይ አራት ዓመት የውኃ ሙሌት የሚደረግለት ከሆነ ለኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ ኢኮኖሚ ድምር በ8 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ይጨምራል ነው የተባለው። ከዚህ መካከል ኢትዮጵያ 6 ነጥብ 79 ቢሊዮን ዶላር በመጨመር ቅድሚያውን እንድትወስድ ያደርጋታልም ተብሏል በመግለጫው። የውኃ ሙሌቱ በአራት ዓመት ውስጥ ቢጠናቀቅ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ አሁን ካለው ዕድገት በ1 ነጥብ 5 ይጨምራል ነው የተባለው። ሱዳንም በ1 ነጥብ 2 በመቶ ዕድገት እንደሚኖራት ነው የተመላከተው።
ከዚህ በላፈ ለሱዳን የጎርፍ መጥለቅለቅ እና በግድቦቿ ሊኖር የሚችለውን ደለለል ይቀንስላታል ነው የተባለው። በግብጽም ቢሆን አስዋን ግድብ ላይ የሚኖረውን የውኃ ትነት ይቀንሳል ተብሏል።
ማኅበሩ ይህን ግድብ በተመለከተ ፊርማ ማሰባሰብ ያስፈለገበት ግብፅ የምታራምደው አቋም ትክክል ስላልሆነና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው ለሦስቱም ሀገራት ስለሆነ ያንን ለማመላከት እንደሆነም አስታውቋል። ፊርማው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሚሠራውን ሥራና የዲፕሎማሲ ሥራውን የሚያግዝ እንደሚሆንም ተገልጿል።
በፊርማ ማሰባሰቡ ሥነ ሥርዓትም 47 ሺህ 57 ኢትዮጵያውን ፊርማቸውን አስቀምጠዋል። ፊርማው በ1 ሺህ 177 ገፅ የኢትዮጵያውያን አቋም በሚያንፀባርቅ መልኩ ለየተመድ ገብቷል ነው የተባለው። የኢኮኖሚውን ማነቆ መቅረፍና የተፈጠረውን ውጫዊ ጫና መመከት ከመንግሥት ብቻ የሚጠበቅ አለመሆኑም በመግለጫው ተነስቷል። ግድቡ ያገባኛል የሚል ኢትዮጵያዊ ሁሉ የበኩሉን ማድረግ አለበት ነው የተባለው። በግብፅና አጋሮቿ ጫና ለመፍጠር እየተሞከረ እንደሆነ ያነሳው መግለጫው ጫናው ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ለማሳዬት የተደረገ ፊርማ መሆኑም ተመላክቷል። ግድቡ የኢትዮጵያ መሆኑን መላው ዓለም እንዲያውቅ ግብፅና አጋሮቿ ያደረጉት ተፅኖ ትክክል አለመሆኑንና በተፅዕኖው ምክንያት ወደኋላ የሚደረግ ነገር እንደማይኖር የሚያሳይ ነውም ተብሏል፤ ፊርማው።
ግድቡ ከገንዘብና ከዕውቀት በላፈ አስፈላጊውን መስዋትነት በመክፈል ዳር ማድረስ የምንችል መሆኑን የሚያሳይ ፊርማ ነውም ተብሏል። ፊርማው ለየተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ እንዲገባ መደረጉም ተመላክቷል። የቀድሞ የቀኝ ግዛት ሐሳብን ለመተግበር የሚፈልጉ አካላት ፍላጎታቸው እንደማይሳካ ለማሳዬት ጥረት ተደርጓልም ተብሏል። ማኅበሩ ለሕዳሴው ግድብ የሚጠበቅበትን ለማድረግ ዝግጁ መሆኑንም አስታውቋል።
ፊርማው ኢትዮጵያ በዓለም ያላትን ተሰሚነት ይጨምራል፣ ግብፅም ወደ ድርድር እንድትመጣ ያድርጋታል ነው የተባለው። ከዚህ ባለፈም በኢትዮጵያ ሐሳብ እንድትገዛ ያደርጋታልም ተብሏል በመግለጫው። ሌሎች አካላትም ተመሳሳይ ድርጊት በማድረግ ጫና መፍጠር እንደሚገባቸውም በመግለጫው ተመላክቷል።
ዘጋቢ:_ ታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ