
ባሕር ዳር፡ መስከረም 26/2013ዓ.ም (አብመድ) በ40ኛው የለንደን ማራቶን ድል ያስመዘገበው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን ዛሬ ረፋድ አዲስ አበባ ገብቷል፤ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት ኮማንደር አትሌት ደራርቱ ቱሉ፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ቢልልኝ መቆያ፣ የኢትዮጵያ አትሌቶች ማኅበር ፕሬዝዳንት ኮማንደር አትሌት ማርቆስ ገነቴና ሌሎችም በቦሌ ዓለማቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ተገኝተው ለቡድኑ አቀባበል አድርገዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ ቁጥር ኢቲ 701 የበረራ ቡድን አባላት የደስታ መግለጫ ኬክ አዘጋጅተው ለአትሌቶቹ ቆርሰዋል፤ የበረራ ትኬታቸውንም ወደ ቢዝነስ ክፍል አሳድገው ወደ ሀገራቸው እንደመለሷቸው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አስታውቋል፡፡
በ40ኛው የለንደን ማራቶን ኢትዮጵያውን በወንዶች የወርቅና ነሐስ እንዲሁም 4ኛ፣ 5ኛ እና 6ኛ ደረጃን በመያዝ ከፍተኛ ድል አስመዝግበዋል፤ በሴቶች ደግሞ 4ኛና 5ኛ ደረጃን ይዘው ማጠናቀቃቸው ይታወሳል፡