ማኅበረሰቡ አሁንም ለኮሮናቫይረስ ልዩ ትኩረት በመስጠት ራሱን እንዲጠብቅ የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አሳሰበ፡፡

127
ባሕር ዳር፡ መስከረም 26/2013ዓ.ም (አብመድ) የኮሮናቫይረስ በኢትዮጵያ ከተገኘ ጀምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ሞተዋል፡፡ ገሚሶቹ አሁንም አልጋ ላይ ናቸው፡፡ የተቀሩት ደግሞ እያገገሙ ወጥተዋል፡፡ የኮሮናቫይረስ በሀገሪቱ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ መንግሥትን ጨምሮ ሲደረግ የነበረው ርብርብ ይበል የሚያሰኝ ነበር፡፡ የ2013 ዓ.ም አዲስ ዓመት ከገባ ወዲህ ግን ለኮሮናቫይረስ የተሰጠው ትኩረት እያነሰ መጥቷል፡፡ በተለይም በነሐሴ 2012 ዓ.ም በሀገር አቀፍ ደረጃ የነበረው የኮሮናቫይረስ ምርመራ ዘመቻ የቫይረሱ ስርጭት ምን ያክል እንደተስፋፋ የሚያሳይ ነበር፡፡ በዚህ ዘመቻ በቀን በሚደረጉ የበርካታ ናሙናዎች ምርመራ ቫይረሱ የተገኘባቸውን በርካታ ዜጎችን መለየት ተችሏል፡፡ ከዘመቻው ወዲህ ግን በሀገር አቀፍ ደረጃ ያለው የመመርመር አቅም ተዳክሟል፡፡ ለዚህም የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በርካታ ምክንያቶችን ጠቅሷል፡፡
በኢንስቲትዩቱ ‘ፐብሊክ ሄልዝ ኢመርጀንሲ ማኔጅመንት ኢመርጀንሲ ኦሬቲንግ ሴንተር ላብ ሴክሽን’ አስተባባሪ ይማም ጌታነህ የኮሮናቫይረስ ኢትዮጵያ ውስጥ እንደገባ በአዋጅ በወጣ መመሪያ ቀጥተኛ ግንኙነት ለሚያደርጉ ባለሙያዎች ክፍያ እንዲፈፀምላቸው ተወስኖ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ ውሳኔው ባልተፈጸመባቸው ክልሎች የባለሙያዎች ተነሳሽነት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳሳደረም ገልጸዋል፡፡ ይህ ጥያቄ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ደረጃ ተጠይቆ ለክልሎች አቅጣጫ ቢቀመጥም አሁንም ያልከፈሉ ክልሎች መኖራቸውን ነው የተናገሩት፤ እናም ክፍያው እንዲፈጸም ክትትል እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል፡፡
በኢትዮጵያ ከሚገኙ 60 የኮሮናቫይረስ መመርመሪያ ላብራቶሪ ማሽኖች 15 ‘‘አቦት’’ የሚባሉ ማሽኖች መሆናቸውን አስተባባሪው ጠቅሰዋል፤ ማሽኖቹ ከተመረቱበት ኩባንያ ውጭ የሚመጣና ለምርመራ የሚያገለግል ኬሚካል እንዳይጠቀሙ ተደርገው መሠራታቸው ማሽኖቹ ሥራ እንዲያቆሙ አድርጓቸዋል፡፡ ማሽኞቹ ከራሱ ድርጅት ካልሆነ በስተቀር በዕርዳታም ሆነ በሌላ መንገድ ከሌሎች ኩባንያዎች የሚመጡ ኬሚካሎችን መጠቀም አለመቻሉን ነው አስተባባሪው ያስረዱት፡፡ ማሽኖቹ በርካታ ናሙናዎችን በቀን የሚመረምሩ እንደነበሩም አስረድተዋል፡፡ ድርጅቱም ኬሚካሎቹን “ከእኔ ካልገዛችሁ በስተቀር አልከፍትም” የሚል ምላሽ መስጠቱን ተናግረዋል፡፡ እናም 50 ሺህ የምርመራ ኪቶች በግዥ ሂደት ላይ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡
እንደአስተባባሪው መረጃ በነሐሴ 2012ዓ.ም በዘመቻ በሦስት ክፍለ ጊዜ 24 ሰዓታት በሙሉ ይሠራ ነበር፤ አሁን ላይ ዘመቻው ሲያበቃ የመሥሪያ ሰዓቱም ስቀለነሰ በቀን የሚመረመረው ናሙና መጠን አነስተኛ ነው፡፡ መርመር ያለበት የኅብረተሰብ ክፍል አለመለየት፣ የናሙና አወሳሰድ እና እየተናበቡ አለመሥራት ችግሮችም እንዳሉ ጠቅሰዋል፡፡ ይህ የሆነበት ደግሞ ቫይረሱ የሚገኝባቸው ሰዎች ቁጥር እየጨመረ በመሄዱ ነው ተብሏል፡፡ እንዚህን ችግሮች ለመፍታትም የሕክምና ክትትል ሊያደርጉ ወደ ጤና ተቋማት የሚመጡ ዜጎችን በመርመር የመመርመር አቅምን ማሳደግና የመለየት ሥራ እንዲሠራ አቅጣጫ መቀመጡን አስተባባሪው አስታውቀዋል፡፡ በአንድ አካባቢ የሚኖሩ እንደ አረጋውያን መርጃ ማኅበራት እና መሰል ተቋማት ላይ ምርመራ የማካሄድ ሥራም ታስቧል፡፡
በዚህ ወቅት ማኅበረሰቡ ስለኮሮናቫይረስ የተሻለ መረጃ እንዳለው የተናገሩት አስተባባሪው ቅድመ መከላከል መልእክቶችን መተግበር ላይ ግን አሁንም በትኩረት መሥራት እንደሚጠበቅ ገልጸዋል፡፡
አቶ ይማም እንዳሉት በኢትዮጵያ አሁን ላይ የኮሮናቫይረስ የሚገኝባቸው ሰዎች 95 በመቶ ከማኅበረሰቡ በሚወሰድ ናሙና ነው፤ ይህ ውጤት የሚያሳየውም ቫይረሱ በኅብረሰተቡ ውስጥ መሠራጨቱን ነው፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመነሳቱ ማኅበረሰቡ ለቅድመ ጥንቃቄ መልእክቶች የሚሰጠው ትኩረት ቀንሷል፡፡ ቫይረሱን ለመከላከል የመንግሥት መመሪያ ብቻ በቂ እንዳልሆነና ዋናውን ሥራ በየግል መሥራት እንደሚገባም አስተባባሪው አስገንዝበዋል፡፡ ማኅበረሰቡም ወረርሽኙን ለመከላከል የሚያደርገውን ጥንቃቄ አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleበተፈጥሮ አደጋ ጉዳት የደረሰባቸው ትምህርት ቤቶች ዘገይተው ሊከፈቱ እንደሚችሉ የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ አስታወቀ፡፡
Next articleበ40ኛው የለንደን ማራቶን በድል የተመለሰው የአትሌቲክስ ቡድን አቀባበል ተደረገለት፡፡