በተፈጥሮ አደጋ ጉዳት የደረሰባቸው ትምህርት ቤቶች ዘገይተው ሊከፈቱ እንደሚችሉ የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ አስታወቀ፡፡

243
ባሕር ዳር፡ መስከረም 26/2013ዓ.ም (አብመድ) ጉዳት የደረሰባቸውን ትምህርት ቤቶች ለመገንባት በሚደረገው ርብርብ ማኅበረሰቡ እና ድርጅቶች እንዲሳተፉም ጥሪ ቀርቧል፡፡
በአማራ ክልል የሚገኙ ሁሉም የ8ኛ እና የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ጥቅምት 9/2013 ዓ.ም ትምህርት ይጀምራሉ፡፡ በትላልቅ ከተሞች ያሉ ትምህርት ቤቶች ደግሞ ጥቅምት 16/2013 ዓ.ም ትምህርት እንደሚጀምሩ ትምህርት ቢሮ አስታውቋል፡፡ ይሁን እንጅ በክልሉ ደቡብ እና ማዕከላዊ ጎንደር ዞኖች 43 ትምህርት ቤቶች በጎርፍ ተጥለቅልቀው አገልግሎት መስጠት የማይችሉበት ደረጃ ላይ ናቸው፡፡ ጉዳት ለደረሰባቸው ትምህርት ቤቶች ዘላቂ መፍትሔ እንደሚያስፈልጋቸው መምህራን፣ ተማሪዎች እና ወላጆች መጠየቃቸውን ጠቅሰን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ ቢሮው ጉዳት የደረሰባቸውን ትምህርት ቤቶች የመለየት ሥራ እየሠራ በመሆኑ መረጃው ተጠናቅሮ እንደተጠናቀቀ ይፋ እንደሚያደርግም ገልጸን ነበር፡፡
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ሙላው አበበ ስለጉዳዩ ተጠይቀው ትምህርት ቤቶቹ ዘገይተው ትምህርት ሊጀምሩ እንደሚችሉ አሰታውቀዋል፡፡ አቶ ሙላው እንደገለጹት በደቡብ እና ማዕከላዊ ጎንደር ዞኖች በሚገኙ 43 ትምህርት ቤቶች በጎርፍ አደጋ ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ በዚህም 28 ሺህ ተማሪዎች የትምህርት ሂደት ላይ ችግር ፈጥሯል፡፡ የ2013 ዓ.ም የሁሉም ትምህር ቤቶች አጠቃላይ የመማር ማስተማር ሂደቱ ቋሚ የጊዜ ሰሌዳ እንደማይኖረው የገለጹት አቶ ሙላው ጉዳት የደረሰባቸው ትምህርት ቤቶችም ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንጻር ዘገይተው ትምህርት ሊጀምሩ እንደሚችሉ አመልክተዋል፡፡
የባከነውን ጊዜ ለማካካስም ከማኅበረሰቡ፣ ከተማሪዎች እና ከመምህራን ጋር በቀጣይ ውይይት እንደሚደረግ አቶ ሙላው ገልጸዋል፡፡ በእነዚህ ትምህርት ቤቶች የሚገኙ የስምንተኛ ክፍል ተማሪዎችን በተለየ መንገድ በሌሎች ትምህርት ቤቶች የማካካሻ ትምህርት የሚያገኙ እንደሚሆን አቶ ሙላው ገልጸዋል፡፡ የትምህርት ቤቶችን ችግር በዘላቂ መንገድ ለመፍታት ከዛሬ ጀምሮ ከአጋር አካላት ጋር በመሆን በልዩ ትኩረት እንደሚሠራም ምክትል ኃላፊው ገልጸዋል፡፡ ማኅበረሰቡ እና ድርጅቶችም በትምህርት ቤቶች ግንባታ ላይ እንዲሳተፉ አቶ ሙላው ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሰራ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ቅድመ ዝግጅቱ በሀገሪቱ ሁሉም ክልሎች ምርጫ እንደሚካሄድ ታሳቢ ያደረገ መሆኑን አስታወቀ፡፡
Next articleማኅበረሰቡ አሁንም ለኮሮናቫይረስ ልዩ ትኩረት በመስጠት ራሱን እንዲጠብቅ የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አሳሰበ፡፡