
“ምርጫ የማናካሂድባቸው አካባቢዎች አሉ የምንልበት ምክንያት የለም” ብለዋል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ፡፡
ባሕር ዳር፡ መስከረም 26/2013ዓ.ም (አብመድ) ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ከጅምሩ ፈታኝ ሁኔታዎች ከፊቱ እየተደቀኑበት ተስተውሏል፡፡ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በበርካታ አካባቢዎች ሰላም እና መረጋጋት ሲርቅ መቅደም ያለበት ሀገራዊ ሰላም ወይስ ምርጫ? የሚለው ጥያቄ ብዙ አነጋግሯል፡፡ የሀገራዊ ሰላም ጥያቄው ሳይፈታ ሌላ ወቅታዊ ክስተት ተፈጠረ፤ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ፡፡ የወረርሽኙን ዓለም አቀፋዊ ስርጭት ተከትሎ ከኢትዮጵያ በፊት 50 የሚደርሱ ሀገራት ምርጫ አራዘሙ፡፡ በኢትዮጵያም የጤና ሚኒስትር ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችል ሁኔታ አለመኖሩን ምክረ ሐሳብ ማቅረቡን ተከትሎ የሕዝብ እንደራሴዎች ምርጫው ላልተወሰነ ጊዜ እንዲራዘም ውሳኔ አሳልፈውም ነበር፡፡
ሀገራዊ ምርጫው በተራዘመበት ባለፉት ስድስት ወራት ከትግራይ ክልል ውጭ በሁሉም ክልሎች ምርጫ አልተካሄደም ነበር፡፡ የትግራይ ክልል ግን የራሱን ‘‘የምርጫ ኮሚሽን’’ ከሕግ ውጭ አቋቁሞ ምርጫ ማካሄዱን እየገለጸ ነው፡፡ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ደግሞ “እንዳልተካሄደ ይቆጠራል” ሲል የትግራ ክልልን እንቅስቃሴ ኢ-ሕገ መንግሥታዊነት አስታውቋል፡፡ ይህንን ተከትሎ አብመድ ‘‘ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ በሁሉም አካባቢዎች ይካሄዳል ተብሎ ይታሰባል?’’ ሲል ላቀረበው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ ሶሊያና ሽመልስ ቅድመ ዝግጅቱ በሀገሪቱ ሁሉም አካባቢዎች እንደሚካሄድ ታሳቢ ያደረገ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሀገሪቱ ሁሉም ክልሎች ምርጫ እንደሚካሄድ ታስቢ ያደረገ የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡ “ምርጫ የማናካሂድባቸው አካባቢዎች አሉ የምንልበት ምክንያት የለም” ብለዋል የኮሙዩኒኬሽን ኃላፊዋ፤ ቢፈጠር እንኳን ሕግና መመሪያን መሠረት አድርገው ወደፊት ለሕዝብ እንደሚገልፁ አመላክተዋል፡፡
ከዚህ ቀደም በነበሩት ሀገራዊ ምርጫዎች በሶማሌ እና በአዲስ አበባ አካባቢዎች ከሀገራዊ ምርጫው በተለየ ጊዜ የተካሄደበት ወቅት እንደነበር የኮሙዩኒኬሽን ኃላፊዋ አስታውሰዋል፤ ተፈጥሯዊ እና ፖለቲካዊ ክስተቶች ቢኖሩ ላይካሄድ የሚችልባቸው አካባቢዎች ሊኖሩ እንደሚችሉም አስረድተዋል፡፡ “ሙሉ በሙሉ በሁሉም አካባቢዎች ምርጫው ይደረጋል ብሎ መሥራት እንጂ መናገር አይቻልም” ነው ያሉት የኮሙዩኒኬሽን ኃላፊዋ በሰጡት አስተያየት፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ