
ባሕር ዳር፡ መስከረም 26/2013ዓ.ም (አብመድ) በደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር በኢንቨስትመንት የተሰማሩ ባለሀብቶች ከ31 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል አስመዝግበዋል፡፡
በተያዘው ዓመት ከ300 በላይ ለሚሆኑ ፕሮጀክቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ለመስጠተ ማቀዱን የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ገለጸ፡፡ ባለፈው ዓመት የ3 ቢሊዮን ብር ካፒታል ላላቸው 112 ኢንቨስትመንቶች ፈቃድ ለመስጠት ታቅዶ ነው ከ245 በላይ ፈቃድ የተሰጠው፡፡ በበጀት ዓመቱ ፈቃድ የተሰጠው ወደ 17 ቢሊዮን ብር ገደማ ላስመዘገቡ ባለሀብቶች ነው፡፡ ከእነዚህም መካከል ወደ 90 በመቶ ገደማ የሚሆኑት በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ የሚሠማሩ መሆናቸውን የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ጽሕፈት ቤት አስታውቀዋል፡፡ በተለይ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ፣ የአልባሳት እና ጨርቃጨርቅ፣ የእንጨት እና ብረታብረት ሥራ፣ የኬሚካል ቅመማ ዘርፎች የተሻለ ተሳትፎ እንዳላቸው የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ ብርሃን ገብረሕይወት አስታውቀዋል፡፡
ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ከግምት ውስጥ በማስገባትም በተያዘው ዓመት ከ300 በላይ የኢንቨስትመንት ፈቃድ ለመስጠት ታቅዷል፡፡ ባለፉት ሁለት ወራትም ለ74 የተለየዩ ፕሮጀክቶች ፈቃድ መሰጠቱ ታውቋል፡፡
በአካባቢው አስተማማኝ ሰላም መስፈን፣ ሰፊ የኢንቨስትመንት አማራጭ እና አስተማማኝ ግብዓት መኖር፣ ማኅበረሰቡ ኢንቨስትመንቱን በባለቤትነት መንከባከቡ እና የመንግሥት ፈጣን መሥተንግዶ መኖር እቅዱን በውጤታማነት ለማሳካት አስቻይ ሁኔታዎች መሆናቸውም ተመላክቷል፡፡
በሌላ በኩል በ2012 በጀት ዓመት የታዩ ክፍተቶችን ለማስተካከል ጠንከር ያለ ግምገማ መደረጉን አቶ ብርሃን አንስተዋል፡፡ በተለይም የመብራትና የውኃ መሠረተ ልማቶች አለመሟላት ቀዳሚ ችግሮች ናቸው፡፡ በከተማ አስተዳደሩ የሚፈቱ ችግሮች በፍጥነት እንደሚስተካከሉ ያነሱት የጽሕፈት ቤት ኃላፊው የመብራት ችግሩ እንዲፈታ ለክልሉ ጥያቄ መቅረቡን አመልክተዋል፡፡
ቦታ አጥሮ ማስቀመጥም ሌላው ችግር ነው፡፡ በከተማዋ ካለው የቦታ እጥረት አንጻር አጥረው የሚቀመጡ ባለሀብቶችን እየተከታተሉ መሬት እየተቀማ ለሌሎች ባለሀብቶች እየተላለፈም ነው፡፡ ባለፈው ዓመት በሊዝ ውላቸው መሠረት ፈጥነው ግንባታ ያልጀመሩ 80 ባለሀብቶችን በመቀማት በፍጥነት ለሚያለሙ ባለሀብቶች መተላለፉ ለዚህ አብነት መሆኑም ተመላክቷል፡፡
በከተማው ከ31 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ 506 ኢንቨስትመንቶች አሉ፡፡ ፕሮጀክቶቹ ሙሉ ለሙሉ ሥራ ሲጀምሩ ከ63 ሺህ በላይ የሥራ እድል ይፈጥራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በኢንቨስትመንት ከተሰማሩት መካከል ደግሞ 300 የሚሆኑት በኢንዱስትሪ ዘርፉ የተሠማሩ ናቸው፡፡ 29 ኢንዱስትሪዎች ምርት የጀመሩ መሆኑን ያስታወቁት አቶ ብርሃን 14 ሺህ የሥራ ዕድል መፈጠሩን ጠቁመዋል፡፡ ይሁን እንጂ የአገልግሎት ዘርፉ ተሳትፎ አናሳ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ