
ባሕር ዳር፡ መስከረም 25/2013ዓ.ም (አብመድ) የኢፌዴሪ ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻል ሂደት አንዱ በሆነው የጨው ምርት ላይ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በአዳማ ከተማ እየመከረ ነው። በመድረኩ የአፋር ክልል የሥራ ኃላፊዎች እና በጨው ማምረት፣ በማቀነባበርና ስርጭት (ንግድ) ላይ የተሰማሩ አካላት ተሳትፈዋል።
በኢትዮጵያ በተወሰኑ ቦታዎች በተደረገ ጥናት 58 ነጥብ 4 ቢሊዮን ሜትሪክ ቶን የጨው ምርት ቢኖርም በሚፈለገው ልክ እየተመረተና ጥቅም ላይ እንዳልዋለ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ተናግረዋል፡፡
የጨው ሀብቱን በዘመነ መንገድ የአመራረት ሂደቱን በማሻሻል፣ አዮዳይዝድ በማድረግና ለገበያ በማቅረብ የሥራ ዕድሉንም ከማስፋት በላይ ለውጭ ገበያም በስፋት ማቅረብ ይቻል እንደነበር ተጠቅሷል።
የጨው ምርት በከፍተኛ መጠን ተመርቶ ወደ ገበያ በመቅረቡ እና ከገበያው ፍላጎት ጋር ባለመጣጣም የአንድ ኩንታል ጥሬ ጨው ዋጋ በአማካይ እስከ 15 ብር ወርዶ እንደነበር በውይይቱ ተነስቷል፤ አምራቾቹ ለከፍተኛ ኪሳራ በመዳረጋቸዉ ምክንያት የግብይት ቦርድ በማቋቋም ጥሬ የጨው ምርት ወደ ገበያ የሚቀርብበት ዋጋ እና መመረት ያለበት መጠን እንዲወሰን መደረጉም ተገልጿል፡፡
በውይይቱ ላይ እንደተነሳው በ2000ዓ.ም እና በ2005 ዓ.ም የተደረጉ የጥሬ ጨው ማምረቻ የዋጋ ግንባታ ሁሉንም የወጪ ርእሶች በዝርዝር ያካተቱ አልነበሩም፤ በ2009 ዓ.ም በተለያዩ ምክንያቶች እያደገ የመጣውን የጥሬ ጨው የማምረቻ ዋጋ መከለስ በማስፈለጉና በአዮዲን የበለፀገ ጨው በፋብሪካ ደረጃ የማቀነባበር ሥራ በመጀመሩ የዳሰሳ ጥናት በማድረግ አዲስ የዋጋ ግንባታ ተሠርቷል፡፡
የኤክሳይስ ታክስ በዋናነት በምርት ላይ የሚጣልበት ምክንያት የመንግሥት ገቢን ለማሳደግ፣ የቅንጦት ነገር ግን መሠረታዊ ፍላጎታቸዉ የማይቀንስና የኅብረተሰቡን ጤና በመጉዳት ማኅበራዊ ችግር በሚያመጡ ምርቶች ላይ ነው ተብሏል፤ በዚሁ አዋጅ የኤክሳይዝ መጠን በተገለፀበት ሰንጠረዥ ተራ ቁጥር አምስት ለጨዉ የተጣለዉ 30 በመቶ ታክስ ለምርቱ የተካተተበት አግባብ ተገቢነትን እና ፍትሐዊነትን ለማረጋገጥ አስቸጋሪ እንደሆነም ተጠቅሷል፡፡ ይህ ክፍያ (ብር 35 ነጥብ 87 በኩንታል) ከአምራቾች ተቀንሶ የሚከፈላቸዉ ቢሆንም ለመንግሥት በተገቢዉ ሁኔታ ገቢ ተደርጎ እንደማያዉቅም ተነስቷል፡፡
በሌላ ወገን የዋጋ ግንባታው በማቀነባበሪያ ቦታዎች የኤክሳይስ ታክስ ሳይካተት በመቅረቱ ማቀነባበሪያዎች ክፍያውን ከተጠቃሚዉ እየሰበሰቡ እና ለመንግሥት ገቢ እያደረጉ ባለመሆኑ መታየት እንዳለበትም ተመላክቷል፡፡ ከሕግ ማዕቀፍ ጀምሮ ግልፅና ተጠያቂነት ያለበት የማበረታቻ፣ የማትጊያ እና የማረሚያ አሠራር ሥርዓት መቅረዕ፣ መተግበር፣ ማስቀጠል እና ማሻሻል አኳያ በፌዴራልም ሆነ በክልሉ መንግሥት የተሠራዉ ደካማ እንደሆነ ተገምግሟል፡፡
የሚወሰዱ ሕጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃዎች በግልጽ ባለመቀመጣቸው በአዮዲን ያልበለፀገ ጨው አዮዲን እንዳለው ሆኖ በኮንትሮባንድ ለተጠቃሚው በከፍተኛ ዋጋ እየቀረበ በመሆኑም ሊስተካከል ይገባዋል ተብሏል፡፡
የአፋር ክልል መንግሥት መቆጣጠሪያ ኬላ በተገቢዉ ቦታ በተለይ ከምርቱ አቅራቢያና በመውጫ በሮች በማስቀመጥ ሊቆጣጠር እንደሚገባም በውይይቱ ተጠቁሟል፡፡
ዘጋቢ፡- እንዳልካቸው እባቡ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m