‘‘የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ፣ ለሕዳሴ ግድብ ግንባታና የእምቦጭ አረምን የመከላከል ሥራ እና ሌሎች የአገራችንን ችግር ለማቃለል ነው ከዚህ የተገኘነው፡፡’’ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ግብረ ኃይል

111

ባሕር ዳር፡ መስከረም 25/2013ዓ.ም (አብመድ) በአሜሪካ የተለያዩ ግዛቶች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሚኖሩበት ቦታ ሆነው ድጋፍ በማሰባሰብ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከያ የሚውል ቁሳቁስ ለጤና ሚኒስቴር አስረክበዋል፡፡

ዶክተር ብርሃኑ ፈለቀ የሚኖሩት በአሜሪካ ሲያትል ግዛት ነው፡፡ ዶክተር ብርሃኑ የኢትዮጵያን ችግር ለማቃለል ከአሜሪካ የመጣው ልዑክ (ግብረ ኃይል) አስተባባሪ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ ለመከላል የምታደርገውን ጥረት ለማገዝ ሎሳንጀለስ በሚገኘው የኢትዮጵያ ቆንስላ አማካኝነት ተደራጅተው ገንዘብ እንዳሰባሰቡ አስረድተዋል፡፡ ከጠቅላላ 49 አባላቱ ስምንት ተወካዮቹን ወደ ኢትዮጵያ የላከው ግብረ ኃይሉ የተለያዩ ሃይማኖት ተከታዮችን በማካተት ኢትዮጵያውያን እና ትውልድ ኢትዮጵያውያን እንዲሁም ኢትዮጵያን የሚወድዱ ሁሉ ድጋፍ እንዲያደርጉ የመጀመሪያ ሥራውን ገንዘብ አሰባስቦ መላክ ማድረጉን አመልክተዋል፡፡

ዶክተር ብርሃኑ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል የሚረዳ የተለያዩ ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጋቸውን ጠቁመዋል፡፡ ‘‘ግብረ ኃይሉ ኢትዮጵያ በአሜሪካ ያሠራችው አዲስ አውሮፕላን ድሪምላይነር 787 ‘ወደ ኢትዮጵያ ይሄዳል’ የሚለውን ዜና ስንሰማ፣ ባዶውን ከሚሄድ ለምን የሕክምና ቁሳቁስ አንልክም በማለት ከልጅ እስከ አዋቂ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል በማሳተፍ ከ200 ሺህ በላይ የአሜሪካ ዶላር የሚያወጣ ቁሳቁስ ገዝተን በማሰባሰብ ለጤና ሚኒስቴር አስረክበናል” ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ የጀመረችው የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የውኃ ሙሊት ስላስደሰታቸው “ለምን የቀረውን አንጨርስም?” በማለት ታላቅ የገንዘብ አሰባሰብ ሥራ መሥራታቸውንም ዶክተር ብርሃኑ ተናግረዋል፡፡

‘‘የአማራ ክልልና የኢትዮጵያ ውበት የሆነው የጣና ሐይቅ በእምቦጭ አረም መበላቱን ስለሰማን ለምን ጣናን አንታደግም? ለምን በጋራ ሆነን ይህ የአገራችን ውበት የሆነውን ጣና ሐይቅን ከእምቦጭ አረም አናድንም?’’ በማለት እምቦጭ አረም ያለበትን ሁኔታ ለማየት ባሕር ዳር ድረስ መገኘታውንም አስታውቀዋል፡፡ ከክልሉ መንግሥት ጋር በመሆን በምን ሁኔታ መርዳት እንደሚችሉ እየተመካከሩ ስለመሆኑም ገልጸዋል፡፡ ‘‘ከዚህ ከተመለስን በኋላ የተለያዩ ቴክኒኮችን ተጠቅመን የድጋፍ ማሰባሰቡን ሥራ እንቀጥላለን’’ ያሉት ዶክተር ብርሃኑ መላ የኢትዮጵያ ልጆች ከጫፍ እስከ ጫፍ ርብርብ እንዲያደርጉ ተግተው እንደሚሠሩ ገልጸዋል፡፡

የእምቦጭ አረምን ለማጥፋት ጎጃም፣ ጎንደር፣ ሸዋ፣ ወሎ፣ ወለጋ፣ ባሌ በሁሉም የኢትዮጵያ አቅጣጫ ያሉት ዜጎች ርብርብ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸውም ዶክተር ብርሃኑ አሳስበዋል፡፡ አረሙን ለማጥፋት የተለያዩ ተሞክሮዎችን በማሰባሰብ ለተግባራዊነቱ እንደሚሠሩም አስረድተዋል፡፡

የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር ፋንታ ማንደፍሮ (ዶክተር) ‘‘እናንተን ወደዚህ ቦታ ያመጣችሁ ልቦናችሁ ነው፡፡ በአዕምሯችሁ ያለውን ሀብታችሁን፣ ዕውቀታችሁን፣ ጊዜያችሁን ሳትቆጥቡ ለወገናችሁ በዚህ ፈታኝ ጊዜ፣ ጊዜያችሁን ብቻ ሳይሆን ሕይወታችሁን ሁሉ ለመሥዕዋት ቆርጣችሁ በመምጣታችሁ የክልላችንም ሆነ የኢትዮጵያ ሕዝብ በእጅጉ ያስታውሳችኋል’’ ብለዋል፡፡

‘‘የሕዳሴ ግድብ ያለ ጣና ሕይወት አይኖረውም’’ ያሉት ዶክተር ፋንታ የጣና ሐይቅ መገኛ አማራ ክልል ቢሆንም የኢትዮጵያ ሀብት እንደሆነና ጣና ከሌለ ዓባይም ሆነ የሕዳሴው ግድብ እንደማይታሰቡም ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም ጣናን ማዳን ማለት ግድቡንም ሆነ ሕይወት ያለውን ፍጡር ሁሉ ማዳን ስለሆነ ጣናን ለመታደግ በሚደረገው ርብርብ በተለይ የእምቦጭን አረም ለማጥፋት በተጨባጭ መፍትሔ ለሚሆን ተግባር ሁሉ የክልሉ መንግሥት አብሮ እንደሚሠራ ገልጸዋል፡፡ “እናንተ በተለያዩ ሀገራት የምትኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን አረሙን ለማጥፋት የምታደርጉትን ሁሉ አብረን ሥራ ላይ በማዋል ለሕዝባችን ተስፋ የሆነ ተግባር እንፈጽማለን” ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያን ችግር ለመቅረፍ ለማገዝ የመጣው ግብረ ኃይል ከጤና እና ትምህርት ሚኒስትሮች ጋር በመተባበር መሰል ችግሮችን ለመፍታት አንግቦ እንደሚሠራም አስረድቷል፡፡

ዘጋቢ፡- ብሩክ ተሾመ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous articleድሮ ቀረ
Next articleየኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን በመከላከል የመማር ማስተማር ሂደቱን ለማስቀጠል በሚያስችሉ ሁኔታዎች ላይ ውይይት እየተካሄደ ነው።