ድሮ ቀረ

186

ባሕር ዳር፡ መስከረም 25/2013ዓ.ም (አብመድ) “በጥዋት ተነስቼ ምጣዱን ስጥድ አባወራው ተነስቶ ድስት ይወዝታል፤ ሽንኩርት ከትፎ ወጥ ይሰራል፤ እኔ እስክጨርስም ቡናውንም አፍልቶ ያቋድሰኛል። ምጣዴን ጨርሼ ስመለስም ተጣጥበን ቁርስ ቢጤ ቀምሰን ወደ እርሻው አብረን እናዘግማለን” በማለት እንኳን በገጠር በከተማው እንኳን ያልተለመደውን የቤት ውስጥ ስራ ከባለቤታቸው ጋር ተጋግዘው እንደሚሰሩ ያጫወቱኝ አርሶ አደር ሀረጌ ወርቁ ናቸው።

“ሴት ወደ ማጀት፤ ወንድ ወደ ችሎት” የሚለውን አባባል ታሪክ ያደረጉት ወ/ሮ ሀረጌና ባለቤታቸው ወደ እርሻ ሲሄዱም የወንዶች ስራ ተደርጎ የሚቆጠረውን የእርሻ ስራም ተባብረው እንደሚሰሩ ባለቤታቸው አርሶ አደር በላቸው እጅጉ እንዳጫወቱን “ወደ እርሻ ቦታው ስንሄድ እኔ ሞፈሩን በአገልግል ከቋጠርነው ቁርስ ቢጤ ጋር እይዛለሁ፤ እሷም ቀንበሩን በትክሻዋ ተሸክማ በሬዎችን ከፊት ከፊት አየነዳች አብራኝ እያወጋን ነው የምናዘግመው” በማለት ነው::

የቤቱ አባወራ በጥዋት ተነስቶ ቁርስ ቢጤ አዘጋጅቶ፣ ቡና፣ ሻይ፣ ወተት… አፍልቶ የፍቅር አጋሩን ቀስቅሶ አብረው ሲመገብ መመልከት ለአብዛኞቻችን የሆሊውድ ፊልም ትይንት ብቻ ነበር። ዛሬ ላይ ግን እንዲህ ያለው የስራ መተጋገዝ እና መተባበር በእኛው መካከል በተለይ በገጠሩ ማህበረሰብ ውስጥ ተጀምሮ አይተናል ብንል ለማመን የሚቸገር አይጠፋም! ግን ሆኗል።
ጥንዶቹ አርሶ አደሮች ወይዘሮ ሀረጌ ወርቁና አቶ በላቸው እጅጉ የሚኖሩት በአዊ ብሄረሰብ አስተዳደር በዳንግላ ወረዳ ውንብሪ ቀበሌ መቅታ ጎጥ ነው። ጎጇቸውን በመመካከርና በመተጋገዝ በአንድ እየመሩት እንደሆነም ጥንዶች በአንድ አይነት ቋንቋ በኩራት ይመሰክራሉ::

ትናንት የእነ ወይዘሮ ሀረጌ ጎጆ የሚመራው በአባወራው ፍቃድ ብቻ ነበር፤ የእሳቸው ይሁንታ ቦታ አልነበረውም ፤እንዲናገሩም አይጠየቁም ነበር። ዛሬ ግን በቤታቸው ሀብትና ንብረት የማዘዝና የመወሰን መብትም እንዳላቸው ተገንዝበዋል። “ባለማወቅ የእኔ የእማ ወራዋ ስራ ብቻ ተደርጎ የነበረውን ስራ ሰውየው ይሰራል:: የእሱ ተብሎ የተተወውንም ስራ አኔ አሳምሬ እየሰራሁ በመተጋገዝ ነው ጎጇችንን ያቆምናት” በማለት ያለፈውን ጊዜ በፀፀት ያስታውሱታል::

ወይዘሮ ሀረጌ “እኔ ልሙት” እያሉ መሀላን በማስቀደም ስለሁኔታው ሲያስረዱ “እኔ ምጣዱን ስጥድ እሱ ድስት ይወዝታል፤ እኔ ድስቱን ከያዝኩለት እሱ ቡናውን አጥቦና ቆልቶ ያፈላል፤ ያጠጣኛልም” ሲሉ የባለቤታቸውን አጋርነት ይገልፁታል። ይህ መተሳሰብና መረዳዳት ፍቅራቸው ከአደር አደር መደርጀቱን ሲያጫውቱን ደስታቸው በፊታቸው ላይ ይነበባል::

ትናንት ዘመድ ጥየቃም ሆነ ለሌላ ጉዳይ እማወራና አባወራው ሲሄዱ ፊትና ኃላ ሆነው እንደሚጓዙ የአብዛኛው ሰው ትዝብት ነው። “ዛሬ ላይ ሰርግም ሆነ ገበያ አልያም ዘመድ ለመጠየቅ ስንሄድ ጎን ለጎን እያወጋን እየተጨዋወትን ነው የምንሄደው” በማለት የሚገልፁት አርሶ አደር ሀረጌ፤ ይህም ሁኔታ ይበልጥ እንድንደማመጥና መተሳሰብና ፍቅር በጎጇችን እንዲሰፍን አድርጓል ይላሉ።

“ከፊታችን በሬዎችን እየነዳን እሱ ሞፈሩን እኔ ቀንበሩን ይዘን ወደ እርሻው ወርደን ስናበቃ አሳምሬ ጠምጃ አርሳለሁ” የሚሉት አርሶአደሯ፤ ይህን በመተባበርና በመተጋገዝ መስራታቸው አረሙ በሰዓት፤ ጉልጓሎው በሰዓት እንዲከወን እንዳስቻላቸው መስክረዋል።

የወይዘሮ ሀረጌ ባለቤት አርሶአደር በላቸው እጅጉ በበኩላቸው “እሷ ምጣድ የምትጥድ ከሆነ እኔ ውሃ አመጣለሁ፤ አቀራርብላታለሁ፤ ድስት የምትወዝት ከሆነ ሽንኩርቱን እከትፋለሁ፣ ቡናም ቆልቼ በመውቀጥ አፍልቼ እንጠጣለን:: ትናንት የቤቱ ስራ የእርሷ ስራ አድርጌ በማሰብ በድያታለሁ:: ዛሬ ጉልበቷን አልበዘብዝም፤ ሌላው ቀርቶ የከብቶችን ጋጣ አስነክቻት እንኳ አላቅሞ:: እራሴው ነኝ የማጠዳው” ሲሉ የትናንትን ራሳቸውን በመውቀስ፤ ዛሬን ደግሞ መተጋገዛቸውን በደስታ ይገልፁታል።

ዛሬ ከባለቤታቸው የተሰወረ ሳንቲም በኪሳቸው እንኳን እንደማይዙ የሚገልፁት አርሶ አደሩ፤ ትንሽ ወጣ ብለው መጠጣት ካማራቸው እንኳን ለባለቤታቸው ነገረውና ተመካክረው ነው። ይህንን በማድረጋቸውም ነው ከትናንቱ ደሳሳ ጎጆ ወጥተው ዛሬ የተሻለ ኑሮ መኖር የጀመሩት:: “ያለፈው አጉል አካሄድ ጎጇችንን ጎድቶታል፤ ዛሬ ባለቤቴ ከአበቁተ ብድር ትሞካክራለች፤ እኔም ያለኝን ከእርሷ ጋር ተመካክረን ነው ሂሳብ የምናወጣው። ሳላውቀውና እሷም ሳታውቀው ምንም የሚወጣም ሆነ የሚገዛ ነገር የለም። በቤቱ ወጭና ገቢ ላይ ባለቤቴ ሀላፊነት አላት። እንደ ትናንቱ በኔ ብቻ የሚደረግ ነገር ዛሬ ላይ አብቅቶለታል። ማታ ላይ ስለ ወጫችን እና ስለሁኔታው እንመካከራለን። ይህ ካልሆ የአባወራ ጫና ጎጆን እያፈረሰ ነውና ትተነዋል” ሲሉም አጫውተውናል።

ጥንዶቹ ሁለት ሴትና ሁለት ወንድ ልጆች አሏቸው:: ከትምህርት ቤት ሲመለሱ ዛሬ ላይ የስራ ክፍፍላቸው ተመሳሳይ ነው። ወንድ ልጁ ወንዝ ወርዶ ውሃ ይቀዳል፤ ሽንኩርት ከትፎ ወጥ ይሰራል፤ ቡሆም ያቦካል። ሴት ልጃቸውም ከአባታቸው ጋር ወደ እርሻ ወርዳ ከማረስ ጀምሮ እስከ አረም እና ጉልጓሎ ድረስ ትሰራለች። ይህ ሁኔታ የተፈጠረው የእነሱን ፈለግ ማየታቸው እንደሆነም አስረድተዋል::

“ቀደሞ ባሉት ጊዜያት ወንድ ልጄን ነበር ወደ ትምህርት የምገፋፋው ሴቲቱን ወደ እናቷ እየገፋው ጋጡንም ቤቱንም ሰንዳ ሰንዳ እንድታደርግ ነበር የምሻው። ዛሬ ግን ተቀይሯል እሷም ከስራ ውጭ ልክ አንደ ወንድሟ እንድትማርና ትምህርቷ ላይ እንድታጠብቅ ነው የምገፋፋት” ሲሉም አርሶ አደሩ ያስታውሳሉ።

አቶ አዲስ ጥላሁን በዳንግላ ወረዳ የውንብሪ ውራፍታ ቀበሌ ዋና አስተዳዳሪ ናቸው። በቀበሌው ስለተፈጠረው የስርዓተ ፆታ እኩልነትና የስራ መተጋገዝ ሲያስረዱ፤ “መጀመሪያ በወረዳው አማካኝነት ስለፆታ እኩልነት በተደጋጋሚ ግንዛቤ ተፈጠረ። በኃላ በሴቶች ላይ የሚደርሰውን የስራ ጫና ለመቀነስ ወንዱ ማጀት ገብቶ የሚስቱን ስራ እንዲያግዝ ማድረግ ቀጠለ። ከዛ ቀላልና ሁሉም የሚሰራው ሆነ፤ እኛም ከምጣድ ጀምሮ ቡናውንም፤ ድስቱንም ሰራን:: ሴቶችም እርሻ ውለው መመለስ ቻሉ:: ከዛ በመተጋገዝ ጎጆ ሲመራ ለውጥ መጣ፤ በየቤቱም የቤተሰብ መቀራረብና ፍቅሩ አየጨመረ ሄደ።

“ቀደም ባለው ጊዚያት አባወራው እርሻ ስራ ወይም መሸታ ቤት አምሽቶ ሲመጣ እማወራ ውሃ አሙቃ እግር ታጥባለች፤ ልጅ አቅፋ ምጣድ ትጥዳለች፤ ድስት ወዝታ ወጥ ትሰራና ውሃ ቀድታ ቡና በማፍላት እራት ታበላለች። ይህ ሁሉ ሲሆን የአባወራው ተግባር ታጥቦ መቅረብ ብቻ ነበር። ይህ ሁኔታ በጎጆው መተሳሰብና መከባበርን አክስሞት ቆይቷል። ዛሬ ግን ሁሉንም ስራ በመተጋገዝ ይከወናል። ባል የሚስቱን እኩልነት አምኖ ተቀብሏል፤ እማወራም በቤቷ አኩል መብት እንዳላት ተረድታ ለአባወራው ያላትን ክብር ሳታጎል እኩልነታን በተግባሯ ታሳያለች” ይላሉ።

እንደ ዋና አስተዳዳሪው ገለፃ ዛሬ ላይ በወንብሪ ቀበሌ መቅታ ጎጥ እማወራ እርሻ ቦታ ወርዳ በሬ ጠምዳ ታርሳለች፤ ከዛም አልፎ ታበራያለች፣ ወንዱም በቤት ሲውል ጥጥ ይፈትላል፣ ሽንኩርት ከትፎ ወጥ ይሰራል። በአጠቃላይ በሴቶች ላይ ይደርስ የነበረው የስራ ጫና ተቃሎ በመተጋገዝ ጎጆ መምራት ተጀምሯል። የሴት የወንድ በሚል በቤት ውስጥ ትንፋሽ እስኪያጥራት ሴቷ ላይ የነበረው የስራ ጫና ተቃሏል። የሴት የወንድ በሚል ተለያይቶ የነበረው ያለመተጋገዝና ያለመረዳዳት ድንበር ተሰብሯል።

በዚህ አይነት መተጋገዝ የህብረተሰቡ ማህበራዊ መተሳሰብ ይበልጥ ጨምሯል፤ የባልና ሚስት ጠብ በእጅጉ ቀንሷል፣ የሴት ልጅ በጊዜ መዳር ቁሟል፣ በእያንዳንዱ ጎጆ የኑሮ መሻሻል እንዲመጣም አግዟል።

አቶ ዘላለም አልማው በዳንግላ ወረዳ ሴቶችና ህፃናት ጽ/ቤት የሴቶች ተጠቃሚነትና ክትትል ባለሙያ ናቸው። በሴቶች ላይ የሚደርሰውን የስራ ጫና ለመቀነስ ለብዙ ጊዜ ስልጠና ሲሰጥ መቆየቱን ያስታውሳሉ። “ ወንዱ ወደ ችሎት ሴቷ ወደ ማጀት” የሚለው የተሳሳተ አስተሳሰብን ለመቅረፍ በወረዳው በሚገኙ 31 ቀበሌዎች በትኩረት እየተሰራ እንደሆነም አሰረድተዋል።
አቶ ዘላለም እንደሚሉት ለገጠሩ ማህበረሰብ በተፈጠረው የስረዓተ ፆታ እኩልነት ግንዛቤ አማካኝነት በሴቶች ላይ የሚደርሰውን የጉልበት ብዝበዛና የስራ ጫና ለማስቀረት በተሰራው ስራ ውጤት ተገኝቷል:: ትናንት አባወራው አምሽቶ መጥቶ ታጥቦ በልቶ መተኛት እና እማወራዋ ሌቱንም አንዴ ልጆች ስታጥብ፣ እቃ ስታነሳሳና ስትደክም አድራ በጥዋቱ ተነስታ ጋጥ ጠርጋ ምጣድ ስትጥድ የነበረበት ጊዜ ተለውጧል። ዛሬ አባወራው በማለዳው ተነስቶ ጋጥ ይጠርጋል፤ ልጆቹን ያጣጥባል፤ ጥጥ ይፈትላል፣ የሚበላ ያበስላል። በዚህ መንገድ ስራን በመተጋገዝ የሴቲቱን የስራ ጫና ማስቀረት ተችሏል።

ትናንት ሴት ልጁን ወደ ማጀት ሲገፋ የነበረው አባወራ ዛሬ ላይ ከወንድ ልጁ አኩል ትምህርቷን እንድትማርና እንድታጠና ማድረግ ጀምሯል። ከወንድሟ ጋር እየተረዳዳች በትምህርቷ እንድትበረታም አባት ዛሬ በብርቱ ሲያግዝ ማየት በአስተሳሰብ በኩል የመጣ ለውጥ እንዳለ በግልፅ የሚያሳይ ነው።

አቶ ዘላለም በማከልም የዚህ ግንዛቤ ማደግ ውጤት ነው በሴቶች ትምህርት ላይም ለውጥ መጧል። ትናንት ወንዱ ብቻ ነበር በልጅነቱ ወደ ትምህርት እንዲሄድ የሚደረገው። ዛሬ ግን ይህን የስረዓተ ፆታ እኩልነትና የስራ መተጋገዝ ላይ በተሰራው ሰፊ ስራ ሴቶች በሰባት አመታቸው ወደ ትምህርት ቤት የሚሄዱት ቀጥር እየጨመረ መጥቷል ብለዋል::

እኛም በእርግጥም የሀገራችን ህዝብ ሃምሳ በመቶ ሴቶች ናቸው፤ የሴቶችን የስራ ጫና በመቀነስና እኩልነታቸውን በማረጋገጥም ዘርፈ ብዙ ተጠቃሚነት አውን ማድረግ ለማህበረሰብ መለወጥ የሚኖረው ፋይዳ የጎላ ነውና መልካም ተግባር ብለነዋል።

በኩር (ግርማ ሙሉጌታ) መስከረም 25 ቀን 2013 ዓ.ም ዕትም

Previous article5ኛው የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤት 6ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ዛሬ ከሰዓት በኋላ ይካሄዳል፡፡
Next article‘‘የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ፣ ለሕዳሴ ግድብ ግንባታና የእምቦጭ አረምን የመከላከል ሥራ እና ሌሎች የአገራችንን ችግር ለማቃለል ነው ከዚህ የተገኘነው፡፡’’ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ግብረ ኃይል