
በትግራይ ክልል የሚገኙ ዐቃቢ ሕጎች በክልሉ መንግሥት የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት እና ባለስልጣናት ፖለቲካዊ ጫና ምክንያት የሥራ ማቆም አድማ ሊያደርጉ ነው።
“ባለብን ከፍተኛ የደኅንነት ስጋት ምክንያት ስማችን አይጠቀስብን” ያሉ አቀቤ ሕጎች ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደተናገሩት የክልሉ መንግሥት የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ሥራቸውንም ኑሯቸውንም እየጎዳው ነው።
የፖለቲካ መሪዎች በደል መገለጫው ብዙ ቢሆንም ዋናው ከሙያ ነጻነት ማጣት እና ከደመወዝ ክፍያ ፍትሐዊነት መጓደል ጋር በተያያዘ ያቀረቡትን ተደጋጋሚ ጥያቄ ከመመለስ ይልቅ ዐቃቤ ሕጎችን ከሥራ ለመቀነስ እየሠሩ መሆኑን ተናግረዋል። በዚህ እና ተደጋጋሚ በሆነው የክልሉ መንግሥት የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ምክንያት ከነገ ጀምሮ የሥራ ማቆም አድማ ሊያደርጉ መሆኑን አብራርተዋል።
በትግራይ ክልል ያሉ ዐቃቤ ሕጎች ደመወዝ በሌሎች ክልሎች ካሉ ተመሣሣይ አቃቤ ሕጎች በጣም ያነሰ ነው። ይህ እንዲስተካከል ቢጠይቁም የክልሉ መንግሥት ቃል ከመግባት ባለፈ ሊያስተካክል እንዳልቻለም ተናግረዋል።
የክልሉ መንግሥት ኢ-ፍትሐዊነት ከሌሎች ክልሎች ዐቃቤ ሕጎች አንጻር ብቻ ሳይሆን በትግራይ ክልል ካሉ ዳኞች ደመወዝም በእጅጉ ያነሰ ነውም ብለዋል።
“ጥያቄያችን ብዙ ነው” ያሉት ዐቃቤ ሕጎቹ “ቅድሚያ በክልሉ በተባባሰው የኑሮ ውድነት ምክንያት እየደረሰብን ያለውን ጫና ለመቋቋም ‘ጥያቄያችን ይመለስልን’ ብለን እንጂ በተቋሙ ላይ ያለው የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ሥራችንን በነጻነት እንዳንሠራ እያደረገን ነው” ሲሉም ተናግረዋል።
የክልሉ መንግሥት ጥያቄያቸውን እንደሚመልስላቸው በመግለጽ አድማውን እንዳይመቱ በመወትወት ላይ እንደሚገኝ የጠቀሱት ዐቃቤ ሕጎቹ በደረሳቸው መረጃ መሠረት ደመወዙን ከማስተካከል ይልቅ የዐቃቤ ሕጎችን ቁጥር ለመቀነስ እየሠራ ነው ብለዋል።
በሥራቸው ላይ በክልሉ መንግሥት እየተደረገባቸው ያለው የፖለቲካ ጣልቃ ገብነትም ለትግራይ ሕዝብ ትክክለኛ ፍትሕ ለመስጠት እንዳዳገታቸው ነው የተናገሩት።
ስለሆነም ቀጣዩ ጥያቄያቸው በተቋማቸው ውስጥ ሙያዊ ነጻነት እንዲከበር ማድረግ መሆኑን ማስታወቃቸውን የኢትዮጵያ ፕረስ ድርጅት ዘግቧል።