ከመዲና አልባነት ወደ ሁለት ቤተ መንግሥት ባለቤትነት …፡፡

320

ባሕር ዳር፡ መስከረም 24/2013ዓ.ም (አብመድ) በአዳል ሱልጣኔት የተነሳው አመፅ እና አዲስ አስተሳሰብ ለማዕከላዊ መንግሥቱ አደጋ ሆኖ ነበር። ከምሥራቁ የተነሳው ማዕበል የቀደመውን እያፈረሰ የራሱን እየሠራ ይሄድ ነበር። ወቅቱ የስልጣን ሽሚያ ብቻም አልነበረም። አዲስ ታሪክ ፅፎ ሌላ መንገድ መጀመር እንጂ። የጣና ሐይቅ በአዕዋፋት ዝማሬ ታጅቦ ተንፈላሷል፤ ጦርነት እንደበረዶ የወረደባት የደምቢያ ምድርን የወባ በሽታ አሳሯን ያበላት ነበር።

ወናግ ሠገድ ገላውዲዎስ አልፈው ወንድማቸው ሚናስ ተተክተው ዙፋኑን ተቀበሉ። ቱርክ ኢትዮጵያን ለመዋጥና እንዳሻት ለማድረግ በቀይ ባሕር በኩል አሰፍስፋ ቀርባለች። የሮም ካቶሊካውያን ደግሞ ሃይማኖታዊ ተልኳቸውን ዓለማቀፋዊ ለማድረግ ‘‘የጦርነት እገዛ እናድርግላችሁ’’ በሚል ሰበብ በኢትዮጵያ ምድር ሃይማኖታዊ ትምህርት ሊያስተምሩ ከጅለዋል። አፄ ሚናስ የወንድማቸውን ስልጣነ መንበር ከተረከቡ በኋላ የካቶሊካውያንን ውትወታ ተወት አድርገው ወደቀይ ባሕር ዘመቱ። ልታስገብር የመጣችውን ቱርክ አስገበሩ። እኚህ ንጉሥ የግዛት ዘመናቸው ሩቅ አልነበረምና ብዙ ሳይቆዩ አለፉ።

የአፄ ሚናስ ልጅ አቤቶ ሠርፀ ድንግል ከዙፋኑ ላይ ተቀመጡበት። በዓለ ሲመታቸውን ወደአክሱም ተጉዘው በፅዮን ማርያም ደጅ አደረጉ። ብልሑ ንጉሥ ውስጣዊ የእነገሥ ተቀናቃኞቻቸውን አደብ አስይዘው ቱርክን ለማስገበር ዘመቱ፤ አስገበሯትም። እስከ ኤደን ባሕረ ሰላጤ ድረስም አስተዳደሩ። በዘመናቸውም ለረጅም ዓመታት የተዘነጋውን የቤተ መንግሥት ግንባታ በጉዛራ ኮረብታ በእንፍራን ባሻገር ጣናን በስተደቡብ እየተመለከቱ ለመቀመጥ በዚያው አሠሩ። ከዘመነ ሮሃ ወዲህ ተንቀሳቃሽ የነበረውን የነገሠታት መኖሪያ ያማረ ቤተ መንግሥት በኖራና ድንጋይ አሠርተው አሳረፉት፤ የመናገሻ ከተማም መሠረቱ። ይህም ቤተ መንግሥት የመጀመሪያው ባለሦስት ሰገነት የአፍሪካ ቤተ መንግሥት እንደሆነ ይነገርለታል። ዘመነ ጎንደርም መንገዱን ጀመረ። አፄ ሠርፀ ድንግልም በ1584ዓ.ም አለፉ። መንበረ ስልጣናቸውንም የወንድማቸው ልጅ የሰባት ዓመቱ ያዕቆብ በእትጌ ስና፣ በመኳንንቱ እና በመሳፍንቱ ታግዘው ያዙት። ልጃቸው ዘ ድንግል የዙፋን ይገባኛል ጥያቄ እንዳያነሱ በግዞት ተላኩ።

ጥቂት ፋታ የሚጠብቁት ካቶሊካውያን በንጉሠ ነገሥት ያዕቆብ ዘመን ሃይማኖታቸውን እንዲያስፋፉ ጥያቄ አቀረቡ። ንጉሡ ያቆብም ሃይማኖታቸውን ስለማስፋፋት ከመነጋገራቸው አስቀድሞ የጦር መሣሪያ ዕርዳታ ከአገራቸው እንዲያመጡና ከዚያ በኋላ እንደሚመክሩበት አስረድተው መለሷቸው። ንጉሡ ያዕቆብ ዕድሜያቸው ከፍ እያለ ሲሄድ ለሞግዚቶቻቸው አልታዘዝ ማለት ጀመሩ። በብልሃት ተይዘውም ወደግዞት ተወሰዱ። የነገሥታቱ ዘር ዙፋኑን ካልያዘ ሕዝቡ አሻፈረኝ ይላል ተብሎ ስለተፈራ ቀደም ሲል በግዞት የነበሩት ዘ ድንግል ዙፋኑን አገኙት።

አፄ ዘድንግል ሃይማኖታቸውን ለማስፋፋት ከመጡት የካቶሊኩ ቄስ ፒያዝ ጋር መልካም የሚባል ወዳጅነት መሠረቱ። እርሳቸውም የካቶሊክን እምነት ተቀበሉ ተባለ። ነገሩ እንግዳ የሆነበት የአገሬው ሰው ተቆጣ። በእርግጥ በንጉሥ ደረጃ እና ካቶሊክ የቤተ መንግሥት ሃይማኖት እንድትሆን ለመጀመሪያ ጊዜ የተቀበሉ የሚባሉት ቆይተው የመጡት ሱስንዮስ ናቸው። በዘድንግል ሐሳብ የተቆጡት የቤተ መንግሥት ባለሟሎች ከቤተ መንግሥት ወጡ። ሠራዊቱም ሁለት ልብ ሆነ። የጦር አበጋዛቸው ራስ ዘሥላሴና እቴጌ ስና (ማርያም ስና ይሏቸዋል) ተቆጥተው ወደደምቢያ ወረዱ። ከእስክንድርያ የመጡት ሊቀ ጳጳሱ አባ ጴጥሮስም ሕዝባቸውን አነቁ። ሕዝቡም ከራስ ዘሥላሴና ከእትጌ ስና ጋር ወገነ። ከንጉሡ ጋር ደግሞ የካቶሊክ ወታደሮች ሃይማኖታችን ከተቀበሉ የሚመጣውን መከራ አብረንወት እንቀበላለን ብለው ወገኑ፤ ጦርነትም ተካሄደ ዘድንግል ተገደሉ።

በግዞት ተይዘው የነበሩት ያዕቆብ ድጋሜ ነገሡ። በሌላ በኩል የገራም ፋሲል ልጅ አቤቶ ሱስንዮስ በአትናትዮስ አማካኝነት ነገሥው ነበር። ሁለቱ ነገሥታትም ተዋጉና ንጉሡ ያዕቆብ ሞቱ። ሱስንዮስም ወደጉዛራ ቤተ መንግሥት ሄደው ሥልጣን ሰገድ ቀደማዊ ተብለው ነገሡ። በንግሥናቸው የመጀመሪያዎቹ ዓመታትም አብያተ ክርስቲያናትን አሠሩ። ከጉዛራ ከነገሡ በኋላም በወደአክሱም ሄደው በፅዮን ደጅ ንጉሠ ፅዮን ተብለው ንጉሣዊ ሥርዓት አከናወኑ። ካቶሊካውያንም ወንጌልን እየተረጎሙ በቤተ መንግሥት ንጉሡን ያማክሯቸው ጀመር። መልካም ወዳጅነት መሠረቱ። በጎርጎራ አጠገብም የማምለኪያ ስፍራ ተበረከተላቸው። ቄስ ፒያዝም ቤተ ክርስቲያን ሠራ። ቄስ ፒያዝ ቤተ ክርስትያን ሲሠራ ንጉሡ አመሥግነው እርሱ ከሠራበት አካባቢ ቤተ መንግሥት እንዲሠራ እና አዲስ ከተማ እንዲመሠረት አዘዙ።

በዚያ ዘመን ከተሠራው ቤተ መንግሥት ውስጥ ነኝ። ፍቅር፣ ቅርስን፣ ታሪክን፣ ትውፊትን፣ እምነትን እና ሃይማኖትን አቅፎ የተኛው ጣና በቀስታ ይወዛወዛል። ጀንበር በምስኮቷ ለመጥለቅ እየገሰገሰች ነው። የፀሐይ ውበት ስትዋጣና ስትገባ ይደምቃል። በማለዳ ከጫጉላ እንደምትወጣ የቤተ መንግሥት ሙሽራ ስትሽኮረመም በፍቅር ልብ ትሰርቃለች። በምሽት ደግሞ ቀለስ መለስ በሚለው ውበቷ ወደመስኮቶቿ ለመግባት ስታዘግም በስስት ትገድላለች። የመጥለቂያ መስኮቷ ከጣና ዳርቻ እንደሆነ ሁሉ በምሽት በጣና ዳርቻ ሆነው ሲመለከቷት ለዋና የምትወርድ መልከ መልካም ቆንጆ ትመስላለች። ወለል ካለው የደምቢያ ምድር በግርጌ በፍቅር ከተኛው ከጣና ሐይቅ ራስጌ ፈጣሪ ለታሪክ ያስቀመጠው ውብ ኮረብታ አለ። ኮረብታው በአብዛኛው የተከለለው በጣና ሐይቅ ነው። በምሥራቅ፣ በደቡብ እና በሰሜን በከፊል ንፍቅ ጣና ያካልለዋልና ነው፤ በስተምዕራብ በኩል የብስ ያካልለዋል። በምዕራቧ በር ዳገትዋን ወጥተው ከቤተ መንግሥቱ ሲደርሱ ሐሴት አለ።

በስፍራው ያገኜናቸው የአካባቢው ተወላጅ እና ታሪክ አዋቂ አቶ ሰጡ አቡሃይ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲወራረድ የመጣውን ታሪክ ለእኔም ነግረውኛል። ‘‘እኔ ጀሮ ጠገብ ነኝ’’ ብለው ነበር የጀመሩልኝ። ጀሮ ጠገብ ማለት ምን ማለት ይሆን? ከአያት ቅድመ አያቶቹ ሲወርድ ሲወራረድ የመጣውን ታሪክ ቁጭ ብሎ ሲሰማ ያደገ እንደማለት ነው አሉኝ። ቤተ መንግሥቱ በ1603ዓ.ም እንደተሠራ የነገሩኝ፤ የቱሪዝም ባለሙያው ኤፍሬም ለገሠም ይሄንኑ አረጋግጠውልኛል። ከጉዘራ ቀጥሎ ሌላኛው ቤተ መንግሥት ነበር። ንጉሠ ነገሥት ሱስንዮስ ይህን ቤተ መንግሥት ለማሠራት ሰባት ዓመታት እንደፈጀባቸው ይነገራል። በሥራውም ሰባት ሺህ ሰዎች ተሳትፈውበታል። በአሻገር የገሊላ ማርያም ቤተ ክርስቲያን ከጣና ሐይቅ ውስጥ ትታያለች።

አካባቢው በወባና ሌሎች ውኃ ወለድ በሽታዎች ይጠቃ ስለነበር ሰኔ ግም ሲል ሐምሌ ሲያጎራ ይቀመጡበት ይሆን ዘንድ ሌላ ቤተ መንግሥት ሳያስፈልጋቸው አልቀረም። ወደደንቀዝ ሄደውም ቤተ መንግሥት አሠሩ። የክረምቱን ወቅት በደንቀዝ ሲያሳልፉ። ሕዳር ሲታጠን ወደጎርጎራ ተመልሰው በዚሁ ቤተ መንግሥት ያሳልፋሉ። ንጉሥ ሱስንዮስ በአንድ የንግሥና ዘመን ሁለት አብያተ መንግሥታትን አሠሩ ማለት ነው።

ቤተ መንግሥቱ ስምንት ያክል ክፍሎች አሉት። በክፍሎቹ ውስጥም የካቶሊክ ቀሳቀውስት ይኖሩበት እንደነበር የቱሪዝም ባለሙያው ኤፍሬም ነግሮኛል። በተለይም ቄስ ፒያዝ ይኖሩባት የነበሩት ክፍል ውብ ናት። ዛሬም ቢሆን ውበቷ ያሳብቃል። በክፍሎቹ 16 ያክል በሮች ነበሩ። ለግቢው ደግሞ ሁለት ትልልቅ በሮች እንደነበሩ ይነገራል። ከቤተ መንግሥቱ መካከል ላይ ደግሞ ቀደም ሲል ቄስ ፒያዝ ያሠሯት የማምለኪያ ስፍራ ቆይቶ ደግሞ የአካባቢው ሰዎች የማርያምን ፅላት አስገብተው ያስቀድሱበት የነበረችው የቤተ ክርስቲያን ፍርስራሽ ይገኛል። በውብ አናፂ በውብ ስፍራ የተሠራ ድንቅ ቤተ መንግሥት። ቤተ መንግሥቱ በምን ያክል ስፍራ ላይ እንዳረፈ እንደማይታወቅ የቱሪዝም ባለሙያው ነግረውኛል። ይሄም ለቤተ መንግሥቱ የተሰጠው ትኩረት አናሳ መሆኑን የሚያሳይ ነው።

በዚህ ቤተ መንግሥት በስተምዕራብ በኩል በሰፊ አጥር የተከለለ ታላቅ ስፍራ አለ። ይህ ስፍራ ንጉሠ ነገሥቱን ለመጠየቅ እና ለእንግድነት ይመጡ የነበሩ ሰዎች ፈረስና በቅሎ ማረፊያ ነው። ንጉሠ ነገሥት ሱስንዮስ ከፖርቱጋል ሚሲዮናውያን ጋር የጠበቀ ቁርኝት በመፍጠር የዘመነች ኢትዮጵያያን ለመገንባት ጥረት አድርገው እንደነበር ይነገርላቸዋል። በቤተ መንግሥቱ ውስጥ ሆነው ሲመሽና ሲነጋ የጣናን ውበት እያዩ በቀኝ እና በግራ መኳንንቱ እና መሳፍንቱ አጅበዋቸው፣ የእልፍኝ አገልጋዮች እንደቄጠማ እያረገዱላቸው፣ በዘመኑ ውብ የሆነው ሽቶ እየተርከፈከፈላቸው፣ ጋሻና ጎራዴ የሰበቁ ጠባቂዎች እንደዓይናቸው ብሌን እየጠበቋቸው፣ የቤተ መንግሥት አጫዋቾች ሳይሰላቹ ለማስደሰት ከበሮ ሲደልቁ፣ ንጉሡ ከዙፋናቸው ቁጭ ብለው በደስታ ስምጥ ሲሉ በዓይነ ኅሊናዬ መጣብኝ። በዚያ ክብር ላይ እኔ የተቀመጥኩበት እስኪመስለኝ ድረስ ያለፈ ክብርና ፍቅር አስታውሼ ደስ አለኝ። ያ ሁሉ መልካም ጊዜ ያ ክብርና ዝና አልፎ በዚያ ዘመን ወርቅ እና አልማዝ ለብሰው በጣና ሰገነት ላይ ሲንጎራደዱ የነበሩት ሁሉ አልፈው አፈር ትቢያ መሆናቸው ትዝ ሲለኝ ደግሞ የሰው ከንቱነት አሳዘነኝ።

ለካ የሰው ልጅ ደስታ በዘመን ድንበር የተከለለ እንደ ፋኖስ መብራት ሲበራ አምሽቶ እኩለ ሌሊት ላይ የሚጠፋ ነው፤ ለካስ በወርቅ የተዋቡት አልፈዋል፤ በአልማዝ ያጌጡት ረግፈዋል፤ አንሸነፍም ያሉት ተሽንፈው ሞተዋል። ከንቱ ውዳሴ ከንቱ ውበት፣ ከንቱ ኩራት ሁሉም አላፊ ጠፊ። ቤተ መንግሦቱን እየተዘዋወርኩ ተመለከትኩ። ትዝታ ብቻ ይዞ በዘመን ቀንበር ተጭኖ ዳግም የግርማ ሞገስ ዘመን እየጠበቀ ተሰይሟል። የፈረስ ግልቢያው፣ የእልፍኝ አሽከሮች ታዛዥነት፣ የእንቢልታው እና የጥሩንባው ድምፅ፣ የግብር አበላሉ ሁሉ የናፈቀው ይመስላል። ከናፍቆት በላይ ውበቱን እያጣ ለመሄድ መቃረቡም ሌላ ሐዘን ነው።

በቤተ መንግሥቱ መግቢያ ወደኮረብታው ሳይወጡ ገና የገሊላ ገዳም መነኮሳት መቀመጫ ወይንም ሞፈር ቤት የሚባለው ይገኛል። ከሐይቅ ዳር የተቀመጡት መነኮሳት የግብርና ሥራ የሚያከናውኑም ነበሩ። በገዳሟ ውስጥ ደግሞ ትጉኃን አበውን ጨምሮ ለአገር ሰላም ለወገን አንድነት የሚጸልዩ አባቶች እንደሚቀመጡ አቶ ሰጡ ነግረውኛል። ‘‘ይኅ ታላቅ ቤተ መንግሥት እንደ ሌሎች ቅርሶች እንክብካቤ ቢደረግለት ኖሮ የሀብት ምንጭ መሆን ይችል ነበር። ታዲያ ምኑን አውግቼህ ልጄ ሀይ ባይ አጥቷል!’’ ነው ያሉኝ አቶ ሰጡ። ቤተ መንግሥቱ ጥገና እና ጥበቃ እንዲደረግለት ብዙ ጊዜ እየተጠዬቀ የሚመደብለት በጀት አናሳ በመሆኑ እዚህ ግባ የሚባል ሥራ እንዳልተሠራለት የቱሪዝም ባለሙያው ተናግረዋል። በእርግጥ በትንሹ እድሳት ሊደረግለት የተቀበረ ኖራ እንዳለ ተመልክቻለሁ። ነገር ግን እየደረሰበት ካለው ጉዳት አንፃር በቂ የሚባል አይደለም። የዞኑ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ጥናት አድርጎ ለጥገና የሚያስፈልገውን ገንዘብ እንደለዬና ለሚመለከተው አካል ለማቅረብ በዝግጅት ላይ እንደሆነበረም ወደስፍራው በሄድኩበት ጊዜ ሰምቻለሁ።

አልፎንሶ ሜንዴዝ ከሮም ካቶሊክ ጳጳስ ሆነው መጡ። ንጉሠ ነገሥቱም ሃይማኖታቸውን ቀየሩ። ነገር ግን የሕዝቡን አመፅ ስለፈሩ ሃይማኖታቸውን መቀየራቸውን መናገር አልፈለጉም ነበር እና ዝምታን መረጡ። ንጉሠ ነገሥቱ ሃይማኖታቸውን ሲቀይሩ እቴጌዋ ወለተሳኅላ በቀደመ እምነታቸው እንደፀኑ ወደ ቆማ አምርተው ቆመ ፋሲለደስ ቤተ ክርስቲያንን አሠሩ። የንጉሡ ሃይማኖት መቀዬር ተደብቆ አልቀረም። በአዋጅ ተነግሮ የካቶሊካዊት ሃይማኖት የቤተ መንግሥት ሃይማኖት እንድትሆን ተደነገገ። የታሪክ ጸሐፊዎች እንደሚሉት ይህ ክስተት ከኢዛና እና ሳይዛና (አብርሃ ወ አፅብሃ ዘመን ጀምሮ የቤተ መንግሥት ሃይማኖት የነበረችውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የቀዬረ ነበር፤ ምንም እንኳን ረጅም ዘመን ባይቆይም።

በቤተ መንግሥት እና በአገር ማስተዳደር ላይ የሲሶ መንግሥት ስልጣን የነበራትን ቤተ ክርስቲያን ሲያገልሉ የተፈራው ሕዝብ ተነሳ። ንጉሠ ነገሥቱን ጠላቸው። ጳጳሱ አልፎንሶ ንጉሡን ከሮማዊት ሴት ጋር አጋብተዋቸው ያልሞተ ሊገዛ የሚል ቃል አስገብተዋቸው ነበር። ካቶሊካዊት ሃይማኖት የቤተ መንግሥት ሃይማኖት እንድትሆን በአዋጅ መነገሩ የመንደር ወሬ የነበረው ግልፅ ሲሆን የለዬለት ጦርነት ተከፈተ፤ ብዙዎች አለፉ። መከራው ፀና። የቀደመው ሃይማኖቴ ተነካ የሚለው አልቻል አለ። ‘‘ሲሱኒዮስ ሆይ ውረድ አጥፍተሃል፣ አቤቶ ፋሲል ሆይ ና ተናፍቀሃል’’ ተባለ።

አቤቶ ፋሲል ወደሕዝቡ ወግነው ነበርና ተወደዋል። ‘‘የሮም ካቶሊክ ትፍለስ ኦርቶዶክስ ትመለስ፣ አቤቶ ፋሲል ይንገሥ’’ የሚለው የፀና አቋም የፋሲልን ወደስልጣን መምጣት አፋጠነው። ሱስንዮስም ዙፋናቸውን ለልጃቸው ለመስጠት ተገደዱ። ንጉሡም ‘‘የቀደመችቱ ሃይማኖት ትመለስ’’ ብለው ተናዘዙ። ሱስንዮስም ታመሙ። ገሚሶች ‘‘ድጋሜ ተጠምቀው ሞቱ’’ ሲሉ ገሚሶች ደግሞ ‘‘በዚያው እንደፀኑ አለፉ’’ ይላሉ። ‘‘ሱስንዮስ የታመሙት የማይደፈረውን ደፍረው ነው’’ እየተባለ ይወራ ስለነበር ፋሲለደስ መነኮሳቱ ምሕላና ጸሎት እንዲያደርጉላቸው ያደርጉ እንደነበርም ተጽፏልም፤ በአፈታሪክም ይነገራል። አለፉም አፅማቸው በታላቁ ገዳም ዳጋ እስጢፋኖስ ተቀመጠ።

አቤቶ ፋሲለደስ ንግሥናውን ተቀብለው አገር ማስተዳደር ጀመሩ። ሕዝቡም የካቶሊክ ሚሲዮናውያን ከቤተ መንግሥት እንዲወጡ ግፊት ፈጠረ። ንጉሡም ቄስ ፒያዝን ጨምሮ በቀይ ባሕር አሻግረው ወደአገራቸው ሸኟቸው። ቄስ ፒያዝም ቀይ ባሕርን ተሻግረው ህንድ ሲደርሱ አለፉ። ፋሲለደስ ጎንደርን ቆረቆሩ። መናገሻም አደረጓት። በዚያ ቤተ መንግሥት አሠራርም ሕዝቡ ሁሉ ተገረመ። ማዕከላዊ መንግሥቱ ተረጋጋ። አዲስ ስልጣኔም መጣ።

ከቤተ መንግሥቱ በስተምሥራቅ በኩል የጣናን ሐይቅ በትዝብት ተመለከትኩት። በፍቅር ወሰደኝ። ልቤ ሲሸበር ተሰማኝ። ወደ ምዕራብም ዞርኩ ሙሽረዋ ጀንበር ልትዋኝ እንደምትወርድ ወይዘሮ ሰበር ሰካ እያለች በእሳት የጋዬ ደን በሚመስለው ዳመና እየተሹለከለች ወደመስኮቷ ለመግባት እየተጣደፈች ነው። የጣና ምዕራባዊ ዳርቻ ቀይ ግምጃ የተነጠፈበት መስሏል። ያን ጊዜ ነበር መምሸቱ ትዝ ያለኝ። በቀስታ ከውቡ ኮሮብታ ወደ ገሊላ ሞፈር ቤት ወረድኩ። በአሻገር እንደመዳፍ ለስልሶ በሚታዬው የደምቢያ ምድር ኅብረ ቀለም ያላቸው ከብቶች በእርጋታ ሳር ሲግጡ ይታያሉ። የማይሻር ትዝታ፣ የማላውቀው ስሜት። ጀንበር ወደመስኮቷ ከመግባቷ አስቀድሜ እኔም ወደማደሪያዬ ለመድረስ ተጣደፍኩ።

ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ

Previous articleገበታ … ቢጀመርስ?
Next article‘ወልቂ’ እና ‘ሃጫሉ’ የተባሉት አዲስ የባቄላ ዝርያዎች የተሻለ ምርት መስጠታቸው ተገለፀ።