ገበታ … ቢጀመርስ?

308

ባሕር ዳር፡ መስከረም 24/2013ዓ.ም (አብመድ) ከመልካም ነገር እንጀምር፤ የቅርብ ጊዜው ሀገራዊ የፖለቲካ ግርሻ ከበረታባቸው ቦታዎች መካከል ግንባር ቀደሙ የአማራ ክልል ነበር፡፡ የሕግ የበላይነት ጠፍቶ፣ የመንግሥት የማስፈፀም አቅም ኮስምኖ እና ሕዝብ በቀየው ተሸማቅቆ አድሮ ለመገናኘት መተማመኛ የጠፋበት ወቅት የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነበር፡፡ የሰላም እጦት ከሚጎዳቸው ማኅበራዊ እና ምጣኔ ሀብታዊ እንቅስቃሴዎች መካከል ደግሞ ቱሪዝም ዋናው ነው፡፡ በየአካባቢው ሰላም ከሌለ እንኳን ከውጭ ከሀገር ውስጥ እንኳን ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ የሚታሰብ አይደለም፡፡ የቱሪዝም ሞተር ደግሞ ተፈጥሯዊ የሆነው የሰው ልጆች እንቅስቃሴ ነው፡፡ አሁን ለተፈጠረው ክልላዊ ሰላም ምስጋና የሚገባቸው በርካቶች ቢኖሩም የክልሉ መንግሥት የፀጥታ መዋቅር፣ የሥራ ኃላፊው እና የሰላሙ ባለቤት ሕዝብ ተቀዳሚ ተጠቃሶች ናቸው፤ ምሥጋና አንድ፡፡

ሌላኛው በጠቅላይ ሚኒስትሩ ‹‹የገበታ ለሀገር›› መርሀ ግብር ከተጎበኘችው የጎርጎራ ወደብ ልማት ጋር ተያይዞ የክልሉ መንግሥት፣ ሕዝብ እና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ያደረጉት ርብርብ ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡ የገበታ ለሀገር መርሀ ግብሩን ተከትሎ በአካባቢው የባለሀብቶች ፍላጎት እየጨመረ መምጣቱን አስተውለናል፡፡ ይህን መከታተል እና ለአፈፃፀሙ ብቁ አመራር መስጠት ብስለት እንደሆነ መቀበልም ግድ ነው፡፡ በክልሉ ርእሰ መሥተዳድር የተመራ ልዑክ በአካባቢው ከሁለት ጊዜ በላይ እንደሄደ እና ከሚመለከታቸው ጋር ውይይት እንዳደረገም አይተናል፤ ምሥጋና ሁለት፡፡ ለእነዚህ ርምጃዎች ዕውቅና መንፈግ ይከብዳል፡፡

ነገር ግን በተፈጠረው መልካም አጋጣሚ ዕድሎችን ማስፋት ደግሞ ይበልጥ ትኩረት የሚሰጠው ቢሆን ተመራጭ ነው፡፡ የአማራ ክልል በርካታ ታሪካዊ እና ተፈሯዊ ቅርሶች ያሉበት አካባቢ ነው፡፡ በዩኒስኮ ከተመዘገቡት ቅርሶች እንኳን የበዙት በአማራ ክልል የሚገኙ ናቸው፡፡ በየአካባቢው ያለው የቱሪስት መስህብ ለቁጥር አታካች ነው፡፡ ከሊማሊሞ እስከ ግሸን፣ ከዘንገና ሐይቅ እስከ ሐይቅ እስጢፋኖስ፣ ከጎንደር ጥንታዊ ቤተ መንግሥታት እስከ ላልይበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፣ ከጣና ሐይቅ ገዳማት እስከ አንኮበር መካነ ነገሥታት፣ ከስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ እስከ ጮቄና ጉና ተራሮች፣ ከጋፋት እስከ መቅደላ፣ ከግሸን እስከ ውቅር መስቀለ ክርስቶስ፣ ከንግሥት ማረፊያ እስከ ሰመርንሃ፣ ከዋልያ አስከ ጭላዳ እነዚህና መሰሎቹን ዓለም ሊያያቸው እና ሊደሰትባቸው የሚሻ የክልሉ ሀብቶች ናቸው፡፡ ‹‹ቱሪዝምን ከባህል ነጥሎ ማየት አይቻልምና›› በየአካባቢው ያለው ማራኪ እና ውብ የባህል ስብጥር ሲታሰብ ደግሞ በክልሉ ከማይጎበኘው ይልቅ የሚጎበኘው ይበረክታል፡፡

ክልሉ ያሉትን የባህል፣ የተፈጥሮ እና የታሪክ ፀጋዎች በማስተዋወቅ እና አልምቶ በመጠቀም ግን አልጀመረውም ማለት ይቀላል፡፡ የመሠረት ድንጋይ ተቀምጦላቸው ያልተጠናቀቁ የቱሪስት ቦታዎችን መቁጠር ቀላል ነው፡፡ እንደመቅደላ አምባ ከሕዝብ የተሰበሰበ ገንዘብ ለተፈለገው ዓላማ ሳይውል የቀረበት መንገድ ያበሳጫል፡፡ ከርእሰ መሥተዳድሩ መሥሪያ ቤት ራስጌ ዕድሳት ተጀምሮ መጠናቀቂያው ምፅዓት የሆነው የቤዛዊት ቤተ መንግሥትም የቱሪስት መዳረሻ ለመሆን ጠያቂ ይሻል፡፡ ዘንገና ሐይቅ የተጀመሩት መዝናኛዎችና የታጠሩት የልማት ቦታዎች የክልሉን መንግሥት ጠንካራ አመራር ሰጭነት ይፈልጋሉ፡፡ ጥገና የሚሹት ቅርሶቻችን የክልሉን የሥራ ኃላፊዎች ጉትጎታ ይማፀናሉ፡፡ መሠረተ ልማት ያልተሟላላቸው መዳረሻዎች ‹‹በእውኑ ባለቤት አለንን?›› የሚሉ ናቸው፡፡

በእርግጠኝነት ‹‹የገበታ ለሀገር›› መርሀ ግብር እንደቋሚ ቢቀጥል እንኳን ክልሉ ይህን የሚያገኘው ያልደረሳቸው ክልሎች ከደረሳቸው በኋላ ነው፡፡ ሀገሪቱ ከቱሪስት የምታገኘውን ገቢ እና ምንጮቹን እንለይ ቢባል ክልሉ ደግሞ እና ደጋግሞ እንደሚደርሰው ቢታወቅም ‹‹ጠባቂነትን›› በሚፀየፍ ሥርዓት እየጠበቁ መቆየት አይመጥንም፡፡ በጎርጎራ የተጀመረውን ‹‹የገበታ ለሀገር›› መርሀ ግብር እየደገፉ ‹‹ገበታ ለአማራ›› በሚል መርሀ ግብርን ማስጀመር ግን ብዙ ባለሀብት፣ ምሁራን፣ አምራች ወጣት፣ … ባለቤት ለሆነው ክልል እና የክልሉ የሥራ ኃላፊዎች የሚከብድ አይደለም፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

Previous articleየቻይና ኩባንያዎች በግብጽ በረሃዎች የዓለም ትልቁን የስኳር ፋብሪካ ለማቋቋም እየሠሩ ነው፡፡
Next articleከመዲና አልባነት ወደ ሁለት ቤተ መንግሥት ባለቤትነት …፡፡