
ባሕር ዳር፡ መስከረም 24/2013ዓ.ም (አብመድ) የወልድያ ዩኒቨርሲቲ በሰሜን ወሎ ዞን ለሚገኙ የእንቅስቃሴ ችግር ያለባቸው አካል ጉዳተኞች አጋዥ የቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል፡፡ ድጋፉ በዞኑ ለሚገኙ ሆስፒታሎች እና በእግር ለመንቀሳቀስ ለሚቸገሩ የአካል ጉዳተኞች የሚያግዝ ነው፡፡
የዩንቨርሲቲው መምህር ፋሲል ንጉሴ (ዶክተር) ተነሳሽነትና ፕሮጀክት አዘጋጅነት አሜሪካን ከሚገኝ የክርስቲያን በጎ አድራጎት ድርጅት የተገኘው የመጓጓዣና የአካል ድጋፍ ቁሳቁስ 240 መሄጃ ወንበር (ዊልቼር)፣ 25 ምርኩዞች (ክራንች) እና 100 የእርምጃ ድጋፎች(ወከር) ሲሆኑ ግምታቸው 1 ነጥብ 3 ሚሊየን ብር እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
‘‘እንደ አንድ መምህር የማኅበረሰብ አገልግሎት ሥራን መሥራት ስለሚጠበቅብኝ የአካል ጉዳተኞችን ችግር መፍታት አንድ የማኅበረሰብ ችግር መፍታት ስለሆነ በዚያ መነሻ ይህ ሐሳብ መጣልኝ” ያሉት ዶክተር ፋሲል ንጉሴ አካል ጉዳተኞችን ከመርዳት በላይ ለኅሊናን የሚያስደስት ነገር አለመኖሩን ገልጸዋል፤ ዩኒቨርሲቲዎችና መምህራን ከመማር ማስተማሩ ጎን ለጎን የማኅበረሰቡን ችግር አጥንቶ የመፍታት ኃላፊነትም ግዴታም እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡
የወልድያ ዩኒቨርሲቲ የጥናትና ምርምር እና ማኅበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ሰሎሞን አበጋዝ (ዶክተር) ዩኒቨርሲቲው አስፈላጊውን የውጪ ግንኙነት በማድረግና ንብረቶቹ ከወደብ ጀምረው የሚጓጓዙበትን ወጪ በመሸፈን እገዛ ማድረጉንም ጠቁመዋል፡ ከዚህ በፊትም በተለያዩ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች የማኅበረሰብ አገልግሎት ሲሰጥ እንደቆየና ይህንኑ አገልግሎቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል፡፡
የመንቀሳቀሻ ተሽከርካሪ (ዊልቼር) ድጋፍ ከተደረገላቸው ውስጥ ወይዘሮ ፀሐይነሽ ደምሴ አስተያዬታቸውን ለአብመድ ሰጥተዋል፡፡ ወይዘሮ ፀሐይነሽ በምርኩዝ (ክራንች) ይጓዙ በነበረበት ጊዜ ይወድቁ፣ ይደክማቸውና በጡታቸው አካባቢ የሕመም ስሜት ይፈጥርባቸው እንደነበር ጠቅሰው የተሰጣቸው ዊልቼር ምቾት ስላለው እንደልብ እንደሚያንቀሳቅሳቸው ገልጸዋል ለተደረገላቸው ድጋፍም አመሥግነዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ዋሴ ባየ – ከወልድያ