“የጎርጎራ ፕሮጀክትን በውጤታማነት ለመተግበር ገቢ መሰብሰብ ላይ ትኩረት ማድረግ ይጠበቅብናል።” ርእሰ መሥተዳድር ተመሥገን ጥሩነህ

198
ባሕር ዳር፡ መስከረም 23/2013ዓ.ም (አብመድ) በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ (ዶክተር) ይፋ ከተደረጉ የገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች መካከል የጉርጎራ ልማት ፕሮጀክት አንዱ ነው። ፕሮጀክቶቹን እውን ለማድረግ ሀብት የማሰባሰብ መርሐ ግብሮች እየተከናወኑ ነው። በጣና ሐይቅ ዳርቻ ላይ የሚገኘውን የጎርጎራ ፕሮጀክትን በውጤታማነት ለመተግበር የሚያስችሉ ሐሳቦችን ለማፍለቅና ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ያለመ ምልከታ የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች አድርገዋል።
የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ተመሥገን ጥሩነህ፣ የሳይንስና ኢኖቬሽን ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶክተር)፣ የፌዴራል መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሀብታሙ ተገኝን (ኢንጂነር) ጨምሮ የክልልና የፌዴራል ከፍተኛ ኃላፊዎች የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሀብታሙ ተገኝ (ኢንጂር) “የበርካታ መስህብ ሀብቶች ባለቤት የሆነውን ጣናና አካባቢውን ለማልማትና ጎብኝዎችን ለመሳብ የረጅም ዔመታት እቅድ ይዞ መሥራት ይገባል” ብለዋል። በገበታ ለሀገር የታቀፈውን የጎርጎራ ልማት ፕሮጀክትን እውን ለማድረግም ዓለም አቀፍ ባለሀብቶችን ማሳተፍ የሚያስችል አሠራር እንዲዘረጋ በትኩረት መሥራት ይኖርብናልም ነው ያሉት።
የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ ወርቁ ኃይለማርያም የገበታ ለሀገር ፕሮጀክት በጎርጎራ እንደሚተገበር ይፋ ከሆነበት ጀምሮ የሚለማውን አካባቢ ከመለየት ጀምሮ ምቹ ሁኔታዎች እንዲፈጠሩ በትኩረት እየሠሩ መሆኑን ነው ያስታወቁት።
“የጎርጎራ ልማት ፕሮጀክትን ለመተግበርና ለጎብኝዎች ምቹ ለማድረግ የአካባቢውን መሠረተ ልማት ማሟላት ዋነኛ ሥራችን ሊሆን ይገባል” ያሉት ደግሞ የአማራ ክልል መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ ደሳለኝ ወዳጆ ናቸው።
የሳይንስና ኢኖቬሽን ሚኒስትሩ አብርሃም በላይ (ዶክተር) በበኩላቸው ለባለሀብቶች ምቹ የመሠረተ ልማት ዝርጋታ እንዲኖር በትኩረት እንደሚሠራ ተናግረዋል።
የጎርጎራ ፕሮጀክት ኃላፊ ፍስሐ አሰፋ (ዶክተር) የጎርጎራ ልማት ፕሮጀክትን በብቃት ለመተግበር ከሙስናና የተንዛዛ አሠራር የወጣ አሠራር መዘርጋት እንደሚጠበቅባቸውና ለተግባራዊነቱም በጥናት ላይ የተመሠረተ ጥረት እንደሚደረግ ገልጸዋል።
የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ተመሥገን ጥሩነህ የጎርጎራ ልማት ፕሮጀክት እንዴትና በምን አግባብ መተግበር አለበት የሚለውን ምሁራንን ያሳተፍ ጥናት በማድረግ ግብዓት እየተሰባሰበ መሆኑን አንስተዋል። የክልሉ የሥራኃላፊዎች ለፕሮጀክቱ የሚውል የወር ደመወዛቸውን ለመስጠት መወሰናቸውን ያስታወሱት ርእሰ መሥተዳድሩ ይህንን ተሳትፎ በማስፋት “ሀብት የማሰባሰብ ተግባሩን ማጠናከር አለብን” ብለዋል።
“የጎርጎራ ልማት ፕሮጀክትን በመተጋገዝ እውን እናደርገዋለን” ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ የሚጠበቀው ገቢ መሰብሰብ ላይ ትኩረት ማድረግ ነው ብለዋል። ለፕሮጀክቱ መተግበሪያ ገንዘብ ለማሰባሰብም የተለያዩ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሀ ግብሮች እንደሚዘጋጁ ነው ርእሰ መሥተዳድሩ ያስታወቁት።
በገበታ ለሀገር ፕሮጀክት 3 ቢሊዮን ብር በማሰባሰብ 3 መዳረሻዎችን ለማልማት ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱ ይታወቃል።
ዘጋቢ:- ስማቸው እሸቴ -ከጎርጎራ
Previous articleየሕግ የበላይነትን በማረጋገጥ የሰብዓዊ መብት ጥሰትን መከላከል እንደሚገባ የሕግ ምሁሩ ጠቆሙ፡፡
Next articleወልድያ ዩኒቨርሲቲ ለአካል ጉዳተኞች የመጓጓዣ ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ።