የሕግ የበላይነትን በማረጋገጥ የሰብዓዊ መብት ጥሰትን መከላከል እንደሚገባ የሕግ ምሁሩ ጠቆሙ፡፡

292

የሲቪል ማኅበራት አይተኬ ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል፡፡

ባሕር ዳር፡ መስከረም 23/2013ዓ.ም (አብመድ) የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ መረጃ እንደሚያመለክተው ሰብዓዊ መብቶች ሰዎች ሁሉ ሰው ሆነው በመፈጠራቸው ብቻ ያገኟቸው መብቶች ናቸው፡፡ በዘር፣ በቀለም፣ በጾታ፣ በቋንቋ፣ በፖለቲካ አቋም፣ በአመለካከት፣ በዜግነት፣ በሀብት ደረጃ ወዘተ ልዩነት አይደረግባቸውም፤ ሰዎች ሰው በመሆናቸው ብቻ ዕውቅና እና ጥበቃ ሊሰጣቸው የሚገቡ፣ ከሰዎች ሰብዓዊ ክብር ጋር በተፈጥሮ የተቆራኙና የማይነጣጠሉ መብቶች ናቸው፡፡

ሰብዓዊ መብቶች በመንግሥት ወይም በማንኛውም አካል የሚሰጡ ወይም የሚከለከሉ አይደሉም፡፡ በሕይወት የመኖር መብት፣ ሐሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት፣ የመዘዋወር መብት ከእነዚህ መብቶች ውስጥ በአብነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ መንግሥት እነዚህን መብቶ ማክበር፣ ማስከበር እና እንዲሟሉ ማድረግ መሠረታዊ ግዴታዎቹ ናቸው፡፡

ከዚህ በተቃራኒ ዜጎች በማንነታቸው እየተመረጡ ጥቃት፣ በደል፣ ዘረፋ፣ ግድያ ሲፈጸምባቸው ይስተዋላል፤ ፖለቲካዊ ለውጡን ተከትሎ የዜጎች በሕይወት የመኖር መሠረታዊ ሰብዓዊ መብት ጭምር ሲጣስ እየተስተዋለ ነው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች የእርስ በርስ ሽኩቻ፣ የማኅበራዊ አንቂዎች የግልም፣ የቡድንም አለመግባባትና ሌሎችም ምክንያቶች ለችግሩ ግብዓት እየሆኑ ነው፡፡

መሠረታዊ ምክንያቶቹ በርካታ ቢሆኑንም የሰብዓዊ መብት ጥሰቱ ለዓመታት ስለ ልዩነት ሲሰበክ መቆየቱና የሕግ ማዕቀፍ ጭምር እንዲኖረው መደረጉ እንደሆነ ያነጋገርናቸው ምሁር ገልጸዋል፡፡ ችግሩን ለመፍታት እና ሰብዓዊ መብቶች የሚከበሩባት፣ አንዱ ላንዱ ስጋት ሳይሆን ጉልበት እንደሆነ በተግባር የሚታይባት እና የጋራ ሀገር መፍጠር እንደሚገባ በወሎ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህሩ ሰሎሞን ጎራው አስረድተዋል፡፡

ይህንን ለማድረግ የሕግ የበላይነትን ማስፈን ወሳኙ ሂደት እንደሆነም ገልጸዋል፡፡ ምክንያቱም የሕግ ዓላማዎች መሠረታዊ ሰብዓዊ መብቶችን ማስከበር፣ ፍትሐዊነትን ማስፈን፣ ግጭቶችን ወይም አለመግባባቶችን መፍታት፣ ሰላምና መረጋጋትን ማስፈን፣ አካባቢያችንን መንከባከብ፣ ሕዝብ ፍላጎት ማስጠበቅ ናቸውና፡፡

እንደ ምሁሩ ማብራሪያ ሀገሪቱ በተስማማችባቸው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች መሠረት ሕጎችን ማሻሻል ይገባል፤ ፖለቲካዊ አለመግባባቶች ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ መፈታት አለባቸው፤ የሕግ የበላይነትን ማስፈን እና ሰብዓዊ መብቶችን ማስከበር የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት በመሆኑ የዜጎችን ግንዛቤ ማሳደግ በትኩረት ሊሠራባቸው ይገባል፡፡ ኅብረተሰቡን በማንቃት እና የሰብዓዊ መብት ጥሰትን በመከላከል ረገድ የሲቪክ ማኅበራት የጎላ ሚና እንዳላቸው የሕግ መምህሩ አቶ ሰሎሞን ተናግረዋል፡፡

ሲቪክ ማኅበራት ራሳቸውን ከፖለቲካና ሌሎች ተፅዕኖዎች በማላቀቅ ለሰው ልጆች ሁሉ መብት መከበር ጥብቅና ሊቆሙ እንደሚገባቸው ገልጸዋል፡፡ እንደ ምሁሩ ማብራሪያ የዓለም አቀፍ የሲቪክ ማኅበራት ትኩረት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ጨምሮ በተለያዩ ዓለም አቀፋዊ ቀውሶች ተጠምዷል፤ በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱ ሲቪክ ማኅበራት በዚህ ወቅት ዘርፈ ብዙ ኃላፊነት ይጠበቅባቸዋል፤ በተለይ የዜጎች መሠረታዊ ሰብዓዊ መብቶች አደጋ ላይ እንዳይወድቁ መሥራት እንዳለባቸው ነው መልእክት ያስተላለፉት፡፡

ዘጋቢ፡-የማነብርሃን ጌታቸው

Previous articleየማንበብ፣ የመጻፍና የማስላት ችሎታ ላላቸው ጎልማሶች ተፈትነው ማስረጃ ሊሰጥ ነው።
Next article“የጎርጎራ ፕሮጀክትን በውጤታማነት ለመተግበር ገቢ መሰብሰብ ላይ ትኩረት ማድረግ ይጠበቅብናል።” ርእሰ መሥተዳድር ተመሥገን ጥሩነህ