
ባሕር ዳር፡ መስከረም 23/2013ዓ.ም (አብመድ) በተቀናጀ የተግባር ተኮር የትምህርት ብርሃን ፈተና በሀገር አቀፍ ደረጃ ሊሰጥ መሆኑን ትምህርት ሚኒስቴር ገለፀ፡፡
ትምህርት ሚኒስቴር በትምህርት ዘርፉ እያካሄደ ካለው የሪፎርም ሥራ ውስጥ የተቀናጀ የተግባር ተኮር ጎልማሶች ትምህርት መሆኑን የትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ጌታሁን መኩሪያ ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ የመጻፍ፣ የማንበብና የማስላት ችሎታ ያላቸውን ጎልማሶችን ለመለየት የሚያስችል በሀገር አቀፍ ደረጃ በተለያዩ ቋንቋዎች የተዘጋጀ የትምህርት ብርሃን ፈተና ሊሰጥ መሆኑን ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡
በፈተናውም ውጤት ያመጡ ጎልማሶች የ3ኛ ክፍል ያጠናቀቁበት አቻ የምሥክር ወረቀት ይዘጋጅላቸዋል ነው ያሉት፡፡
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በትምህርት ዘርፉ እየተካሄዱ ባሉ ሪፎርሞች ላይ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ጋር ምክክር እያካሄደ መሆኑን በማኅበራዊ ገጹ አስታውቋል፡፡