‹‹የምርጫውን ደረጃ የምናሻሽለው ምርጫውን ለማስዋብ ሳይሆን ለተአማኒነቱ መሠረት ስለሆነ ነው፡፡›› ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

280

ባሕር ዳር፡ መስከረም 23/2013ዓ.ም (አብመድ) ኢትዮጵያ እና ምርጫ ትውውቃቸው ከ67 ዓመታት በላይ ይዘልቃል፡፡ በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት የወጣውን የ1947 ዓ.ም ሕገ መንግሥት መሠረት ያደረገ ነበር፤ ነገር ግን ንጉሡን እና ሴኔታቸውን (የላይኛውን) ምክር ቤት ያላካተተ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ምርጫ በ1949 ዓ.ም ተጀምሮ ነበር፡፡ ዘውዳዊው መንግሥት ምንም እንኳን ሕገ መንግሥት አርቅቆና አጽድቆ ምርጫ ቢጀምርም የሕዝቡን ተሳትፎ እና የስልጣን ባለቤትነት ማስፋት ባለመቻሉ በአብዮታዊ ደርግ ሊተካ ግድ ሆነበት፡፡

በሶሻሊዝም የፖለቲካዊ ርዕዮተ ዓለም የተጠመቀው ወታደራዊ ደርግ ደግሞ ምርጫ ቢያደርግም ቅሉ ተመራጮቹ ሁሉ ከአንድ ወንዝ የተቀዱ ነበሩ፡፡ አብዮታዊ ደርግ የሚሳሳለትን ርዕዮተ ዓለም እንደሚነጠቅ ስለሚሰጋ መድበለ ፓርቲ ብሎ ነገር አይሰማም ነበር፡፡ ከደርግ ውድቀት በኋላ በኢትዮጵያ መንበረ ስልጣኑን የተቆናጠጠው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲ ግንባር (ኢሕአዴግ) የመጣበት ወቅት ዴሞክራሲ በዓለም ሀገራት በተንሰራፋበት ወቅት ቢሆንም ዕድሉን የተጠቀመበት ግን አይመስልም፡፡

በ1983 ዓ.ም ጀምሮ ስልጣን የያዘው ኢሕአዴግ አምስት ጊዜያት ያክል ምርጫ ቢያካሂድም፤ መድበለ ፓርቲን ፈቅጃለሁ ቢልም ‹‹የይስሙላ›› ከመባል የወጡ ግን አልነበሩም፡፡ መቶ ከመቶ ማሸነፍ ብርቅ ያልነበረባቸው ምርጫዎች በተካሄዱባቸው ዓመታት በተቃዋሚዎች ተፈተነ ከተባለ እንኳን በ1997ቱ ምርጫ ነበር፡፡ ምንም እንኳን ድህረ ምርጫ ‹‹ጨዋታ ፈረሰ›› ዓይነት ቢመስልም፡፡ በዘመነ ኢሕአዴግ የተካሄዱት አምስቱም ምርጫዎች በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ ነጥብ የሚጥሉት ደግሞ ‹‹ዓለማቀፍ ደረጃቸውን ያልጠበቁ›› በሚል ክስ ነበር፡፡

ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ የዓለማችን ወቅታዊ ክስተት በሆነው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በሕዝብ እንደራሴዎች እንዲራዘም ውሳኔ ተላልፎ ነበር፤ ነገር ግን ቫይረሱ በቶሎ ሙሉ በሙሉ የመጥፋት ዕድል እንደማይኖረው መታመኑን ተከትሎ እና የጤና ሚኒስትር ምክረ ሐሳብን ተቀብሎ ምክር ቤቱ ምርጫው እንዲካሄድ የወሰነው በቅርቡ ነበር፤ ምንም እንኳን ቀኑ በግልፅ ባይታወቅም፡፡

ምርጫው በተራዘመባቸው ወቅቶች የዝግጅት ሥራው እንዳላቋረጠ የተናገረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በተለይም የምርጫውን ደረጃ ያሻሽላሉ ያላቸውን የቁሳቁስ ግዥ እያጠናቀቀ መሆኑን ጠቁሟል፡፡ 2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ከመንግሥት ካዝና እና ቀሪውን ደግሞ ቦርዱ በጥረቱ ከዓለም አቀፍ ለጋሾች አፈላልጎ 3 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ማጽደቁ ይታወሳል፡፡ ‹‹ብሩ በዝቷል›› እየተባለ ይተች የነበረው ምርጫ ቦርዱ የምርጫውን ደረጃ ለማሻሻል የተቀመጠው በጀት ምክንያታዊ እንደሆነም ሲገልፅ ተደምጧል፡፡

‘‘ሀገራዊ ምርጫን ብቁ የሚያደርጉ በርካታ ጉዳዮች ቢኖሩም ገለልተኛ ተቋም እና በቂ ግብዓት ወሳኝ ናቸው’’ ያሉት የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ ሶሊያና ሽመልስ ናቸው፤ ከዚህ አንፃር ከኮሮናቫይረስ መከሰት በፊት የተመደበው በጀት ምክንያታዊ እንደነበር ይሞግታሉ፡፡ ነገር ግን የኮሮናቫይረስ ክስተት ነባራዊ ሁኔታውን ብቻ ሳይሆን የበጀት ፍላጎትን ሊቀይረው እንደሚችል አመላክተዋል፡፡ የእንደራሴዎች ውሳኔ ምርጫው ለቫይረሱ በማያጋልጥ መልኩ እንዲካሄድ ስለሚያዝዝ የመራጮች ምዝገባ፣ የመራጮች ትምህርት፣ ስልጠናዎች እና የምርጫው ሂደት ኮሮናቫይረስን ታሳቢ ያደረገ ስለሚሆን ተጨማሪ በጀት መጠየቁ እንደማይቀር አመላክተዋል የኮሙዩኒኬሽን ኃላፊዋ፡፡

እንደ ኮሙዩኒኬሽን ኃላፊዋ ገለፃ በአንድ ምርጫ ጣቢያ እስከ አራት የሚደርስ የድምፅ መስጫ ሳጥን ቢያስፈልግ በሚል 207 ሺህ የድምፅ መስጫ ሳጥን እና 50 ሺህ 900 የድምፅ መስጫ ኪት ግዥ ተፈጽሟል፡፡ የተቋሙን የቴክኖሎጂ መሠረተ ልማት ዝርጋታ ለማዘመን ጥረት ተደርጓል፡፡ መመሪያዎች፣ የማሰልጠኛ ቁሳቁስ እና የመራጮች ትምህርት ሕገ ደንቦች የኮሮናቫይረስን ታሳቢ ባደረገ መንገድ እየተሻሻሉ ነው፡፡

ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ ውስጥ የተካሄዱት ምርጫዎች ዝቅተኛ የሚባለውን ዓለም አቀፍ ደረጃ እንኳን እንደያሟሉም ወይዘሪት ሶሊያና ተናግረዋል፤ ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ቢያንስ ዝቅተኛ እና መሠረታዊ ደረጃውን ያሟላ ለማድረግ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡ ከዚህ ቀደም የተካሄዱት ሀገራዊ ምርጫዎች ኮሮጆዎች ሳይቀር ሀገር ውስጥ የተሰፉ፣ የድምፅ መስጫ እና የመራጮች መመዝገቢያ ከክላስር ሚዘጋጁ ነበሩ፡፡ ‹‹ይህንን ያክል የምርጫውን ደረጃ የምናሻሽለው ምርጫው ለማስዋብ አይደለም፡፡ የምርጫው ደረጃ መሻሻል ለተአማኒነቱ መሠረት ስለሆነ ነው›› ብለዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

Previous articleበአረጋውያን ስም የሚነግዱ አካላት ክትትል ሊደረግባቸውጰ ይገባል ተባለ።
Next articleየማንበብ፣ የመጻፍና የማስላት ችሎታ ላላቸው ጎልማሶች ተፈትነው ማስረጃ ሊሰጥ ነው።