የኩላሊት እጥበት ሕክምና በቁሳቁስ እጥረት እየተፈተነ ነው፡፡

178

ባሕር ዳር፡ መስከረም 23/2013ዓ.ም (አብመድ) በቁሳቁስ እጥረቱ ምክንያት ለእንግልት እና ለተጨማሪ ወጪ መጋለጣቸውን በባሕር ዳር ፈለገ ሕይወት አጠቃላይ ሪፈራል ሆስፒታል የኩላሊት እጥበት ታካሚዎች ተናግረዋል፡፡ ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ በሳምንት ሦስት ጊዜ ሕክምናው ሲደረግላቸው የነበሩት አቶ ስለሺ ከቅርብ ጊዜያት ወደዚህ እጥበቱን የሚያገኙት ሁለት ጊዜ፣ አንድ ጊዜ ከዚያም አለፍ ሲል በሁለት ሳምንት እንደሆነ አንስተዋል፤ አቶ ሶሎሞን አዕምሮም በተመሳሳይ፡፡ ከ30 እስከ 100 ብር ይገዙት የነበረ መድኃኒት ከመንግሥት ሆስፒታል ባለመገኘቱም ከ800 እስከ 1 ሺህ ብር እንዲያወጡ እንዳደረጋቸው ገልጸዋል፡፡ ከሚያወጡት ከፍተኛ ወጪ ተጨማሪ እንዲያወጡ ከማድረጉም ባለፈ በጤናቸው ላይ ከፍተኛ ጫና እየደረሰ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም መንግሥት ችግሮቹን እንዲያስተካክልላቸው ጠይቀዋል፡፡

የአማራ ክልል የኩላሊት ሕሙማን ማኅበር የሕዝብ ግንኙነት ተወካይ ዶክተር ቢያድጌ አስቻለ እንዳሉት ደግሞ በፈለገ ሕይወት አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሪፈራል ሆስፒታል በሕክምና ቁሳቁስ እጥረት ምክንያት ሕሙማን ሦስት ገዜ የኩላሊት እጥበት እንዲያደርጉ ቢመከርም ሁለት እና አንድ ጊዜ ብቻ ሲሠራላቸው ቆይቷል፡፡ ሆስፒታሉ አዲስ የኩላሊት ሕመምተኞችን መቀበል ካቆመም ስድስት ወራት አልፈውታል፡፡

ዶክተር ቢያድጌ እንደገለጹት በየሳምንቱ ደግሞ ከሁለት እስከ ሦስት ታማሚዎች በአልጋ እና በማጠቢያ ማሽን ችግር ምክንያት ሕክምና ሳያገኙ ወደየቤታቸው ይመለሳሉ፡፡ ሆስፒታል ደርሰው ከሚመለሱት ባሻገርም በሌሎች ሪፈራል ሆስፒታሎችና የገጠር ሆስፒታሎች የቦታ እጥረት እንዳለ የሚነገራቸው በርካታ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡ ለዓመታት በማሽን ታግዘው ሽንታቸውን የሚሸኑ እና ሌሎች ሕሙማን የሕክምና ችግር እየገጠማቸው መሆኑንም ነው ዶክተር ቢያድጌ ያነሱት፡፡

በተመሳሳይ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል ‘‘አሲድ ኮንሰንትሬተር፣ ባይካርቦኔት፣ ዲያላይዘር፣ ብለድ ላይን፣ ፌስቱኒድል’’ እና ሌሎችም የሕክምና ቁሳቁስ እጥረት መኖሩን የሆስፒታሉ የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስትና የኩላሊት ሕክምና ሰብስፔሻሊስት ወርቃገኘው ኃይሉ (ዶክተር) አስታውቀዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ችግሩን መፍታት እንዲቻል የቀጥታ ግዥ እያከናወነ የተወሰነ ለውጥ መኖሩንም አንስተዋል፡፡

የፈለገ ሕይወት አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሪፈራል ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር የሰውበላይ ምናለ (ዶክተር) በሰጡት ምላሽ የቁሳቁስ እጥረቱ የተፈጠረው በአቅራቢዎች ቁጥር ማነስ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የኩላሊት ሕክምና ቁሳቁስ ፍላጎት ማደጉን የገለጹት ዶክተር የሰውበላይ የአቅርቦት እጥረት መኖሩን አስታውቀዋል፡፡ በዚህም ሆስፒታሉ ታካሚዎችን ለማስተናገድ ተቸግሮ ነበር፡፡ አሁን ላይ ግን የግብዓት ቀርቦት ችግሩ ተቀርፎ የተሟላ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ይሁን እንጂ አቅርቦቱ አስተማማኝ እንዳልሆነና በድጋሚ እንዳይቋረጥም ተሰግቷል፡፡

ማኅበረሰቡ በየጊዜው የኩላሊት ምርመራ ስለማያደርግ በአማራ ክልል ምን ያህል የኩላሊት ሕሙማን እንዳለ በግልጽ አይታወቅም፡፡ ዶክተር ቢያድጌ የዓለም ጤና ድርጅት ከ2017 እስከ 2019 ያወጣውን መረጃ ዋቢ አድርገው እንደተናገሩት በየዓመቱ ከ10 ሰዎች መካከል አንዱ ለበሽታው ተጋላጭ ይሆናል፡፡ በዚህ ጊዜ 35 ሕሙማን በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል፤ 47 ሕሙማን ደግሞ በፈለገ ሕይወት አጠቃላይ ሪፈራል ሆስፒታል መደበኛ የኩላሊት እጥበት እየተደረገላቸው ይገኛሉ፡፡ 480 ለእጥበት ያልደረሱ ድንገተኛ የኩላሊት ሕመምተኞች ደግሞ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሕክምና እየተደረገላቸው ነው፡፡ እጥበት ደረጃ ላይ ያልደረሰ ድንገተኛ የኩላሊት ሕመም ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ መሆኑንም ዶክተር ወርቃገኘው ኃይሉ ተናግረዋል፡፡

ማኅበሩ በኩላሊት ሕክምና ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት በሥራ ላይ ያሉትን ሁለት የኩላሊት እጥበት ማዕከላት ወደ ሰባት ለማሳደግ እየሠራ ይገኛል፡፡ ለዚህም ፕሮፖዛል መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡ እያንዳንዱ ማዕከል ከሦስት እስከ አምስት የኩላሊት እጥበት ማሽኖች ቢኖራቸው እንኳን መርዛማ ነገሮችን ወስደው የሚታመሙ እንዲሁም በወሊድ፣ በኢንፌክሽን እና በሌሎች ምክንያቶች ለሚከሰት ድንገተኛ የኩላሊት ሕመም ፈጣን ሕክምና ለመስጠት ያስችላል፡፡

የሕክምና ቁሳቁስ ችግሮችን መፍታትም የማኅበሩ የዕቅድ አካል ነው፡፡ በእንቅስቃሴው በውጪ ሀገራት የሚኖሩ በተለይም በሙያው የሰለጠኑ ኢትዮጵያውያን ጥሩ ተሳትፎ በማድረግ ላይ መሆናቸው ተመላክቷል፡፡ ማኅበሩም ከጤና ቢሮ እና ከሆስፒታሎች ጋር ተቀናጅቶ እንደሚሠራ ዶክተር ቢያድጌ ተናግረዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ

Previous articleከግማሺ ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ለምረቃ ወደ ኮሌጅና ዩኒቨርሲቲ ሊጠሩ ነው፡፡
Next articleበአረጋውያን ስም የሚነግዱ አካላት ክትትል ሊደረግባቸውጰ ይገባል ተባለ።