በአረጋውያን ስም የሚነግዱ አካላት ክትትል ሊደረግባቸውጰ ይገባል ተባለ።

222

ባሕር ዳር፡ መስከረም 23/2013ዓ.ም (አብመድ) በአማራ ክልል በሁሉም አካባቢዎች የገቢ ማስገኛ እንዲኖር እየተሠራ መሆኑን የአማራ ክልል የአረጋውያን ማኅበር አስታወቀ፡፡ ማኅበረሰቡ በተናጠል የሚያደርገውን ድጋፍ መዋቅራዊ ማደረግ እንደሚገባም የባሕር ዳር ከተማ የአረጋውን ማኅበር ገለጿል፡፡

በአማራ ክልል ለአረጋውያን ገቢ እያስገኘ ያለው በባሕር ዳር የሚገኘው የአረጋውያን የገቢ ማስገኛ ሕንጻ ብቻ ነው፡፡ ሕንጻው 7 ሚሊዮን ብር ዓመታዊ ገቢ ያስገኛል፡፡ ከዚህ ውስጥ 6 ሚሊዮን ብር ገደማ በቀጥታ ለአረጋውያን ድጋፍ ይውላል፡፡ 1 ሺህ 500 አረጋውያን ብቻ በየወሩ የ300 ብር ድጋፍ ይደረግላቸዋል፡፡

በአማራ ክልል 1 ነጥብ 29 ሚሊዮን አረጋውያን እንዳሉ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ወደ 60 በመቶ የሚሆኑት አረጋውያን ደግሞ የሰው እጅ ጠብቀው የሚተዳደሩ ናቸው፡፡ ይህም ገና ብዙ መሥራት እንደሚገባ የሚያመላክት ነው፡፡

የማኅበሩ ፕሬዝዳንት ነጻነት ደስታ እንዳሉት በክልሉ በ13 ዞኖች የገቢ ማስገኛ አንዲኖር እየተሠራ ነው፡፡ 10 ማኅበራት ቦታ መረከባቸውንም ገልጸዋል፡፡ በደሴ ከተማ አስተዳደር አምስት ማኅበራት ለገቢ ማስገኛ ግንባታ የሚሆን ወደ 7 ሚሊዮን ብር ገደማ ማሰባሰባቸውንም አመላክተዋል፡፡ በተመሳሳይ ሞጣ ከተማ አስተዳደር ላይ የገቢ ማስገኛ ግንባታ እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡ እነዚህ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴዎች ከተጠናከሩ የአረጋውያንን ችግር ለመቀነስ ጉልህ ሚና አላቸው ተብሏል፡፡

“አንድ ሺህ ኪሎ ሜትር በአንድ እርምጃ ይጀመራል” ያሉት አቶ ነጻነት ጅምሩ ተስፋ ሰጪ ቢሆንም ብዙ መሥራት እንሚያስፈልግ አመላክተዋል፡፡ አብዛኛው አረጋውያን ድጋፍ እያገኙ አለመሆኑን በመግለጽም በአንድነት መተባበር እንደሚገባ መክረዋል፡፡

የክልሉሉ ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ በአዋጅ በተሰጠው ስልጣን እና ኃላፊነት መሠረት ጥሩ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝም አመላክተዋል፡፡ ነገር ግን በአረጋውያን ስም ለሚደራጁ አካላት የሚሰጠው ዕውቅና ሊፈተሽ እንደሚገባው አንስተዋል፡፡ አንዳንዶቹ ከአረጋውያን ማኅበሩ የገንዘብ ድጋፍ መጠየቃቸውን እንደማሳያ በመጥቀስም ዕውቅና ሲሰጥ ቀጣይነታቸው ሊረጋገጥ እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡ “በአረጋውያን ስም የሚነግዱ አካላት ሀይ ሊባሉ ይገባል” በማለትም ፈቃድ ከመከልከል ጀምሮ የመከታተልና የማረም ሥራ እንዲሠራ አሳስበዋል፡፡

የባሕር ዳር ከተማ የአረጋውን ማኅበር ምክትል ሰብሳቢ ደሳለኘ ካሳሁን እንዳሉት መንግሥት የአረጋውያንን ጉዳይ የሚከታተል ዳይሬክቶሬት ዘርግቶ እንቅስቃሴ መጀመሩ ለማኅበሩ ጥሩ ዕድል ፈጥሯል፡፡ ድጋፍ እንዲያገኙም የድርሻውን እየተወጣ ነው፡፡ ማኅበሩ ለአባላቱ ቅድሚያ ቢሰጥም ለማንኛውም አረጋዊ ድጋፍ እደረገ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን የአቅም ውስንነት እንዳለበት አንስተዋል፡፡

ማኅበረሰቡ አረጋውያንን በብዛት የሚደግፈው በዓላት ሲደርሱ ብቻ ነው፡፡ ይህም ወጥነት እንደሌለው በመግለጽ ድጋፉ በዘላቂነት እንዲቀጥል መዋቅራዊ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡ ለዚህም በተበታተነ መልኩ ድጋፍ የሚያደርጉ ሰዎች ከማኅበሩ ጋር ተቀራርበው እንዲሠሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ‹አረጋውያንን በዘላቂነት መደገፍ የራስን ቤት ለነገ መሥራት ነው› በማለትም ድጋፉን መዋቅራዊ ማድረግ ማኅበሩን ራሱን የማስቻል ሚና እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡ የባሕር ዳር ከተማ አረጋውያን ማሕበር 2 ሺህ 500 ቋሚ አባላት አሉት፡፡

ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ

Previous articleየኩላሊት እጥበት ሕክምና በቁሳቁስ እጥረት እየተፈተነ ነው፡፡
Next article‹‹የምርጫውን ደረጃ የምናሻሽለው ምርጫውን ለማስዋብ ሳይሆን ለተአማኒነቱ መሠረት ስለሆነ ነው፡፡›› ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ