
ባሕር ዳር፡ መስከረም 23/2013ዓ.ም (አብመድ) በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የትምህርት መርሐ ግብር አቋርጠው የነበሩ 530ሺ የኮሌጅና ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ለማካካሻ ትምህርት እና ለምረቃ በጥቅምት ወደ ተማሩባቸው ተቋማት ሊመለሱ መሆኑን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል። ዩኒቨርሲቲዎችም ‹‹ተማሪዎችን ለመቀበል ተዘጋጅተናል›› ብለዋል።
በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር ደቻሳ ጉርሙ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል እንዳብራሩት ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ከሚማሩባቸው ተቋማት ርቀው ነበር። አሁን ባለው ሁኔታ ግን ተማሪዎችን ዳግም መጥራት አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል። ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ሥጋት ጋር በተያያዘ ከትምህርት ገበታ ርቀው የነበሩ ተማሪዎችን ለመቀበልና ያለፈውን የትምህርት ዘመን ለማካካስ ከወዲሁ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል።
እንደአቶ ደቻሳ ገለፃ፤ 270 ሺህ የሚሆኑ በተለያዩ ደረጃ ትምህርታቸው ይከታተሉ የነበሩ የቴክኒክና ሙያ ተማሪዎች፣ 260 ሺህ የመጀመሪያ ዲግሪ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ርቀው የቆዩ ሲሆን የምረቃ መርሐ ግብሩ መካሄድ ከነበረበት ወቅት የዘገየ በመሆኑ እነዚህ ተማሪዎች በጥቅምት ወደ ሚማሩበት ተቋም የሚመለሱ ይሆናል፤ የትምህርት ክፍለ ጊዜውንም ለማካካስ የተለያዩ ሥራዎች በቀጣይ ይከናወናሉ። በመቀጠልም በ2013ዓ.ም ወደ ዩኒቨርሲቲ ትምህርት መግባት የሚጠበቅባቸው ተማሪዎች ጥሪ እንደሚደረግ ጠቁመዋል።