በጎርፍ አደጋ ጉዳት የደረሰባቸው ትምህርት ቤቶች ዘላቂ መፍትሔ እንደሚያሻቸው መምህራን፣ ተማሪዎች እና ወላጆች ተናገሩ፡፡

201
ባሕር ዳር፡ መስከረም 23/2013ዓ.ም (አብመድ) በጎርፍ ተጥለቅልቀው ጉዳት ለደረሰባቸው ትምህርት ቤቶች ዘላቂ መፍትሔ እንደሚያስፈልጋቸው መምህራን፣ ተማሪዎች እና ወላጆች ጠይቀዋል፡፡ በደቡብ ጎንደር ዞን ፎገራ ወረዳ ዋገጠራ ቀበሌ ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች እንደገለጹት ጣና ሞልቶ አካባቢው በመጥለቅለቁ በእንጨት የተሠሩ ትምህርት ቤቶች ፈርሰዋል፤ መጻሕፍትን ጨምሮ የተለያዩ የመማሪያ ግብዓቶች ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡
ውባንተ አዳነ እና ነጠሩ በዋገጠራ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ8ኛ ክፍል ተማሪዎች ናቸው፡፡ ተማሪዎቹ እንደገለጹት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ እንደ ሀገር በትምህርታቸው ላይ ተፅዕኖ ቢያሳድርም በዚህ ወቅት ደግሞ በጣና ሐይቅ መሙላት በደረሰው የውኃ መጥለቅለቅ በአካባቢው የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ፈራርሰዋል፤ የመማሪያ ቁሳቁስ ወድመዋል፤ አካባቢውም በእምቦጭ አረም ተወርሯል፡፡ በዚህም ምክንያት እስከዚህ ወቅት ድረስ በትምህርት ቤቱ ምዝገባ አለመጀመሩ ስጋት እንደፈጠረባቸውም ተማሪዎች ገልጸዋል፡፡ በተለይም ደግሞ የ8ኛ ክፍል ተማሪዎች ወደ አጎራባች ትምህርት ቤቶች ትምህርታቸውን የሚጀምሩበትን ሁኔታ እንዲመቻችላቸው ጠይቀዋል፡፡
በዋገጠራ ቀበሌ የተማሪ ወላጅ መንገሻ ወንዴ እንደነገሩን በአካባቢው በደረሰው የውኃ መጥለቅለቅ በእንጨት የተሠሩት ትምህርት ቤቶች ፈራርሰዋል፤ ንብረቱም ወድሟል፡፡ በዚህም የ8ኛ ክፍል ተማሪ ልጃቸው እስከዚህ ወቅት ድረስ አለመመዝገቡና በኮሮናቫይረስ ወረርሽን ምክንያት ከባከነው ጊዜ በላይ ችግሩ አሳሳቢ እንደሆነባቸው ተናግረዋል፡፡ መንግሥት ተማሪዎች ተመዝግበው ከሌሎች ተማሪዎች ጋር ትምህርታቸውን እንዲጀምሩ ከማድረግ ባለፈ የተጎዱ ትምህርት ቤቶችን ዘላቂ መፍትሔ ሊያስቀምጥላቸው እንደሚገባም ጠይቀዋል፤ የወደሙ የትምህርት ግብዓቶችን የመተካት ሥራ ሊሠራ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
በፎገራ ወረዳ የዋገጠራ አንደኛ ደረጃ ሙሉ ሳይክል ትምህርት ቤት ርእሰ መምህር ጌታሰው ፋንታ እንደገለጹት በአደጋው ምክንያት ማኅበረሰቡ ወደ ተለያዩ አካባቢዎች በመበታተኑ በቀላሉ ተማሪዎችን አግኝቶ ለመመዝገብ መቸገራቸውን ገልጸዋል፡፡ በውኃ የተጥለቀለቀው አካበቢ ወደ ነበረበት ካልተመለሰ ለምዝገባ እንደሚቸገሩም ነግረውናል፡፡ ይህም የ8ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ለሚወስዱ ተማሪዎች ችግር እንደፈጠረባቸው አስታውቀዋል፡፡ በትምህርት ቤቱ በእንጨት የተሠሩ ዘጠኝ የመማሪያ ክፍሎች እና ቤተ መጻሕፍ ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ ለእነዚህ ትምህርት ቤቶች ትኩረት ሰጥቶ ዘላቂ መፍትሔ መስጠት ካልተቻለ ችግሩ ቀጣይነት እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡ በዋገጠራ አንደኛ ደረጃ ሙሉ ሳይክል ትምህርት ቤት የሚገኙ 1 ሺህ 481 ተማሪዎች እስከዚህ ወቅት ድረስ ምዝገባ አለመጀመራቸውን ርእሰ መምህሩ ገልጸዋል፡፡ የደቡብ ጎንደር ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ ያዜ ሀብቴ በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጡን በስልክ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም፡፡
በሌላ በኩል የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ መስፍን ርካቤ እንደገለጹት ደግሞ በዞኑ በምሥራቅ ደምቢያ እና ጎንደር ዙሪያ ወረዳዎች በሚገኙ ዘጠኝ ትምህርት ቤቶች በውኃ መጥለቅለቅ ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ 5 ሺህ 494 ተማሪዎችም ተፈናቅለዋል፡፡ በሁለት ትምህርት ቤቶች ላይ ደግሞ ሙሉ በሙሉ ጉዳት መድረሱን አቶ መስፍን ነግረውናል፡፡ ውኃው ወደ ነበረበት እስኪመለስ ድረስ ተማሪዎች በአጎራባች ትምህርት ቤቶች እንዲማሩ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡ ለዚህም ማኅበረሰቡን፣ አደጋ መከላከል ምግብ ዋስትና እና ልዩ ድጋፍ የሚሹ አካባቢዎች ማስተባበሪያ ኮሚሽንና ሌሎች ድርጅቶችን በማስተባበር ጊዜያዊ የመማሪያ ክፍሎችን ለመገንባት እየተሠራ እንደሚገኝም አቶ መስፍን ነግረውናል፡፡ ጉዳት በደረሰባቸው ትምህርት ቤቶች የተማሪዎች ምዝገባ መከናወኑንም ኃላፊው አስታውቀዋል፡፡
ከክልሉ ትምህርት ቢሮ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው በማዕከላዊ እና ደቡብ ጎንደር ዞኖች በሚገኙ 43 ትምህርት ቤቶች በውኃ መጥለቅለቅ ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ በዚህም 28 ሺህ ተማሪዎች የትምህርት ሂደት ላይ ችግር ፈጥሯል፡፡ የመማሪያ ቁሳቁስም ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ አብመድ በክልሉ በተፈጥሮ አደጋ ጉዳት የደረሰባቸውን ትምህርት ቤቶች ዘላቂነት ጉዳይ አስመልክቶ የትምህርት ቢሮን ምላሽ ለማካተት ጥረት አድርጓል፡፡ ቢሮው ጉዳት የደረሰባቸውን ትምህርት ቤቶች የመለየት ሥራ እየሠራ በመሆኑ መረጃው ተጠናቅሮ እንደተጠናቀቀ ይፋ እንደሚያደርግ ገልጧል፡፡
ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሰራ
ፎቶ፡ ከፋይል
Previous articleመርጌታ በላይ አዳሙ ከጣና ሐይቅ “የእምቦጭ አረምን የሚያጠፋ መድኃኒት አለኝ” የሚሉት መድኃኒት አነስተኛ እና ውጤታማ አለመሆኑ ተገለፀ።
Next articleከግማሺ ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ለምረቃ ወደ ኮሌጅና ዩኒቨርሲቲ ሊጠሩ ነው፡፡