መርጌታ በላይ አዳሙ ከጣና ሐይቅ “የእምቦጭ አረምን የሚያጠፋ መድኃኒት አለኝ” የሚሉት መድኃኒት አነስተኛ እና ውጤታማ አለመሆኑ ተገለፀ።

584

ባሕር ዳር፡ መስከረም 23/2013ዓ.ም (አብመድ) ኅብረተሰቡ መርጌታ በላይ አዳሙ ከጣና ሐይቅ የእምቦጭ አረምን ለማጥፋት የሚረዳ መድኃኒት አለኝ የሚሉትን መድኃኒት ውጤታማ አለመሆኑን ተገንዝቦ አረሙን ለመጥፋት እንዲዘጋጅ ጥሪ ቀርቧል።

ባሕር ዳር ዩኒቨርሰቲ እና የተለያዩ የምርምር ተቋማት ቴክኒካል ኮሚቴ አዋቅረው ሲከታተሉት የነበሩት የመርጌታ በላይ አዳሙን ሥራ በተመለከተ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል። ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በመግለጫው ላይ የተገኙት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ተስፋዬ ሽፈራው (ዶክተር) “መርጌታ በላይ አዳሙ ለመጀመሪያ ጊዜ ለሙከራ የሠሩት የእምቦጭ አረም ማጥፊያ መድኃኒት በአነስተኛ ደረጃ አረሙን ማጥፋት ቢቻልም የጎንዮሽ ጉዳቱ በሳይንስናዊ ምርም አልተረጋገጠም” ብለዋል። የላብራቶሪ ሥራ ለመሥራትም መርጌታው ተቀራርቦ ለመሥራት የሚያስችል ዕድል እንዳልሰጡ ገልጸዋል።

አሁንም “አለኝ” የሚሉትን መድኃኒት ውጤታማ አለመሆኑን ተረድተው በቀጣይ የመንግሥት ተቋማት የማንንም ዕውቀት ያለ ባለቤቱ መብት እና ፈቃድ መውሰድ የማይፈልጉ መሆናቸውን አውቀው ሳይንሳዊ ሂደቶችን ተከትሎ ሌላ ዕድል እንዲሞክሩ ዶክተር ተስፋዬ አሳስበዋል። ገለልተኛ አካል ይዘው ዕውቀታቸውን ለአገር ማበርከት ከቻሉ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የማመቻቸት ሥራ ለመሥራት ፈቃደኛ እንደሆነም ተቁመዋል። “በመጓተት ለጣና ሐይቅ ጥፋት ከመሆን ልማት መሆን ቢቻል መልካም ነው” ብለዋል። ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ለመርጌታ በላይ አዳሙ መድኃኒት የውሳኔ ሐሳብ እንዳልሰጠም ተናግረዋል።

የጣና ሐይቅ እና ሌሎች የውኃ አካላት ጥበቃ ልማት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አያሌው ወንዴ (ዶክተር) “የመርጌታ በላይ ጉዳይ ኅብረተሰብ ወደ ቀልቡ ተመልሶ ጣናን ከእምቦጭ እንዳይከላከል እያደረገ ነው” ብለዋል። በ2013ዓ.ም በኅብረተሰቡ ጉልበት እና በማሽን ውጤታማ ሥራ ለመሥራት የሚደረገውን ጉዞም እያደናቀፈ እንደሚገኝ ተናግረዋል። “ከእምቦጭ ጋር ወዳጅነት የለንም። በእምቦጭ የምንኖር ሰዎች አይደለንም” ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ “በአሉቧልታ ጊዜያችን ባይጠፋ መልካም ነው” ብለዋል።

መርጌታ በላይም “አግኝቻለሁ” የሚሉት መድኃኒት ውጤታማ አለመሆኑን በአገር ውስጥና በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውን እንዲረዱም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል። “መርጌታ በላይ ከዕፅዋት የቀመሙትን የእምቦጭ አረም መድኃኒትም ከዩኒቨርስቲ፣ ከግብርና ምርምር እና ከዓሳ ዘርፍ ተማራማሪዎችን ቴክኒካል ኮሚቴዎችን በማዋቀር ክትትል ተደርጓል” ነው ያሉት። ውጤታማ ባለመሆኑም ለሙከራ ሥራቸው የምሥጋና ደብዳቤ እንደተሰጣቸውና ለወደፊትም ከፍ ያለ ሥራ ሠርተው ከመጡ አብሮ ለመሥራት ከመርጌታ ጋር መነጋገራቸውን በጋዜጣዊ መግለጫ ተናግረዋል። ለሥራው ሲመጡ ግን ሳይንሳዊ መርህን ተከትለው፣ ለቴክኒካል ኮሚቲ ፕሮፖዛል አቅርበው መሆን እንዳለባቸው ተናግረዋል።

ከባሕር ዳር ዓሳ ምርምር ማዕከል በኮሚቴነት ከሠሩት መካከል አቶ አዳነ መላኩ አንዱ ናቸው። የመርጌታ ሥራ ሳይንሳዊ መንገዱን ተከትሎ የተሠራ ባይሆንም ዓረሙን በመጠነኛ ደረጃ ማጥፋቱን ተናግረዋል። ነገር ግን በውስጡ የሚገኙ ትንንሽ ነፍሳትን እንደሚገድልም ገልጸዋል። “ዓሳ ላይ ችግር ባያደርስም ሰዎች ሲመገቡት ሊኖር የሚችለው ተፅዕኖ አልታየም” ብለዋል፡፡

የእምቦጭ አረም ማጥፊያ እንደፈጠሩ የሚናገሩት መርጌታ በላይ አዳሙ ግን በመግለጫው ሐሳብ አይስማሙ፤ መግለጫው ሲሰጥ ሊጠሩ ይገባ እንደነበርም አመላክተዋል፡፡ መድኃኒቱ ከዕፅዋት ብቻ የተቀመመና በብዝኃ ሕይወት ላይም ጉዳት የማያደርስ መሆኑን ለአብመድ ተናግረዋል፡፡ በቀጣይ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና ተመራማሪዎች በተገኙበት በሳይንሳዊ መንገድ ተፈትሾ ውጤቱ እንዲረጋገጥ እንደሚፈልጉም መርጌታ በላይ ተናግረዋል፡፡

ዘጋቢ፡- አዳሙ ሺባባው

Previous articleበኢትዮጵያ 60 በመቶ የሚሆኑት አረጋውያን ጧሪ እና ደጋፊ የላቸውም ሲል ማኅበሩ አስታወቀ።
Next articleበጎርፍ አደጋ ጉዳት የደረሰባቸው ትምህርት ቤቶች ዘላቂ መፍትሔ እንደሚያሻቸው መምህራን፣ ተማሪዎች እና ወላጆች ተናገሩ፡፡