በኢትዮጵያ 60 በመቶ የሚሆኑት አረጋውያን ጧሪ እና ደጋፊ የላቸውም ሲል ማኅበሩ አስታወቀ።

440

ማኅበረሰቡ አረጋውያንን ከችግር እንዲታደጋቸው የአማራ ክልል አረጋውያን ማኅበር ጥሪ አቀረበ። ማኅበሩ ይህንን ያለው ዛሬ የዓለም አረጋውያን ቀንን በኢትዮጵያ ለ29ኛ ጊዜ በባሕር ዳር ሲያከብር ነው። የማኅበሩ ፕሬዝዳንት ነጻነት ደስታ እንዳሉት በኢትዮጵያ ወደ 60 በመቶ ገደማ የሚሆኑት አረጋውያን ጧሪ እና ደጋፊ የላቸውም። ለሀገራቸው ጋሻ መከታ ሆነው የነበሩት እነዚህ አረጋውያን በየቤተ እምነቱ እና በየጎዳናው በልመና ላይ መሠማራታቸውንም አስታውቀዋል።

ማኅበሩ በባሕር ዳር በ10 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያሠራው የአረጋውያን ገቢ ማስገኛ ሕንጻ ለ1 ሺህ 500 አረጋውያን በየወሩ 300 ብር ይረዳል። ይህ ግን ካለው የአረጋውያን ቁጥር አንጻር በቂ አለመሆኑ ተመላክቷል። የ1 ሺህ 500 አረጋውያንን መሠረታዊ ፍላጎትም አያሟላም። ቀጣይ በየዞኑ ተመሳሳይ መሥራት ከተቻለ ግን የተሻለ ድጋፍ ማድረግ እንደሚቻል ነው የማኅበሩ ፕሬዝዳንት የተናገሩት። ይህንን ለማድረ ማንኛውም የኅብረተሰብ ክፍል አረጋውያንን ለመታደግ እጁን ሊዘረጋ እንደሚገባም ጥሪ አቅርበዋል። ሁሉም ለአረጋውያን ክብር፣ ጥቅም እና መብት መጠበቅ የድርሻውን እንዲወጣም አሳስበዋል።

የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አማረ ዓለሙ ከተማ አስተዳደሩ አረጋውያንን በመንከባከብ ሂደት የድርሻውን እንደሚወጣ ተናግረዋል። በከተማ አስተዳደሩ የሚከናወኑ የልማት ሥራዎች ከአረጋውያን መብት እና ጥቅም አኳያ የሚከናወን እንደሚሆን ተናግረዋል።

የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ በዓሉ ሲከበር የዕድሜ ባለጸጎች ያበረከቱትን አስተዋዕጾ ለመዘከር፣ በዕድሜያቸው ያካበቱትን ዕውቀት እና ልምድ ለወጣቱ ትውልድ ለማስተላለፍ እና በእርጅና ምክንያት ደጋፊ ያጡ አረጋውያንን ማኅበረሰቡ እንዲንከባከብ ለማስታወስ በማሰብ መሆኑን ገልጧል። የቢሮው ምክትል ኃላፊ ጥላሁን መኳንንት አረጋውያን ለኢትዮጵያ ሰላም በማስጠበቅ ላበረከቱት ጉልህ ሚና ዕውቅና ሊሰጣቸው እንደሚገባም አንስተዋል።

በሕይወታቸው ላይ ተፅዕኖ የሚያደርሱ ጉዳዮችን በመፈተሽ ወቅታዊ ምላሽ በመስጠት ተገቢ መሆኑንም አንስተዋል። ለዚህም የአረጋውያንን የመብት ጥሰት፣ ጥቃት እና አድሏዊ አሠራርን ማስቆም፣ ገቢ የሚያስገኛቸው ድጋፍ ማድረግ እንደሚጠይቅ ገልጸዋል።

ከቢሮው በተገኘ መረጃ መሠረት በኢትዮጵያ የአረጋውያን ቁጥር እየጨመረ ይገኛል። በ2007 ዓ.ም የሕዝብ እና ቤት ቆጠራ ዋቢነት የሀገሪቱ የአረጋውያን ቁጥር 3 ነጥብ 6 ሚሊዮን መሆኑን አስታውሰዋል። ከዚህ ውስጥም 1 ነጥብ 29 ሚሊዮን ገደማው በአማራ ክልል የሚገኙ ናቸው። በመሆኑም ለአረጋውያን የሚሰጠው ምላሽ በዚያው ልክ መሆን እንደሚገባው አመላክተዋል።

ቀኑ “ወቅታዊና ተግባራዊ ምላሽ ለአረጋውያን” በሚል መሪ ሐሳብ በኢትዮጵያ ለ29ኛ ዛሬ በባሕር ዳር ከተማ ተከብሯል። በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች በልዩ ልዩ ተግባራት ታስቦ መዋሉንም ቢሮው አስታውቋል። በበዓል አከባበሩ ላይ የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት አባላት፣ አረጋውያን እና ልዪ ልዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።

ዘጋቢ:- ደጀኔ በቀለ

Previous articleየበረሃ አንበጣ መንጋን ለመከላከል በርጭት ላይ የነበረች ሄሊኮፕተር በወረባቦ ወረዳ ተከሰከሰች፡፡
Next articleመርጌታ በላይ አዳሙ ከጣና ሐይቅ “የእምቦጭ አረምን የሚያጠፋ መድኃኒት አለኝ” የሚሉት መድኃኒት አነስተኛ እና ውጤታማ አለመሆኑ ተገለፀ።