በ2013 በጀት ዓመት ለመሠረተ ልማት ግንባታዎች ከ5 መቶ ሚሊዮን ብር በላይ በጀት መያዙን የከተማ አስተዳደሩ አስታወቀ።

196

የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት 4ኛ ዙር ምርጫ 8ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 20ኛ መደበኛ ጉባኤ ዛሬም ቀጥሎ ውሏል።

በዛሬ ውሎው ከምክር ቤት አባላቱ ለተነሱ ጥያቄዎች ማብራሪያና ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል። በዋናነት የመሠረተ ልማት ችግሮች ጥያቄ ቀርቧል። በተለይም በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር የንጹሕ መጠጥ ውኃ ችግር አሳሳቢ እንደሆነ ተነስቷል።
የውኃና ፍሳሽ አገልግሎት ጽሕፈት ቤቱ ሥራ አስኪያጅ ይርጋ ዓለሙ ከ1994 ዓ.ም ጀምሮ ለከተማው ነዋሪ ውኃ እየቀረበ ያለው ከከርሰ ምድር እንደሆነ አስታውቀዋል። ሆኖም አሁንም አቅርቦቱና ፍላጎቱ እንዳልተመጣጠነ አስረድተዋል። የኤሌክትሮ ሜካኒካል ችግር እንዳለም ጠቁመዋል። የውኃ ፓምፖች የጥራት ችግር እንዳለባቸው ሥራም አስኪያጁ አስገንዝበዋል።

የውኃ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ትልልቅ ፕሮጀክቶች እንደሚያስፈልጉም አቶ ይርጋ ጠቁመዋል፤ በክልሉ ውኃ መስኖና ኢነርጂ ልማት ቢሮ አማካኝነት እየተሠራ ያለው የጥቁር ውኃ ፕሮጀክት የሲቪል ሥራው መጠናቀቁን ሥራ አስኪያጁ ጠቅሰዋል። ሙሉ በሙሉ ሲገባደድም ችግሩን ያቃልለዋል ተብሎ እንደሚጠበቅ አብራርተዋል።

እንደኃላፊው ምላሽ በጃፓን መንግሥት ድጋፍ እየተገነባ ያለው ፕሮጀክት በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መከሰት ምክንያት ተቋርጧል፤ ነገር ግን በቅርብ ጊዜያት ውስጥ ግንባታው ይቀጥላል፡፡

የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አማረ ዓለሙ በአጠቃላይ መሠረተ ልማት ክንውኖች ላይ መዘግየት ወይም በጊዜ ሥራዎችን የመፈጸም ችግር እንዳለ አሳውቀዋል። በቀጣይም ድክመቱን በማስተካከል መቀጠል እንዳለባቸውም ገልጸዋል፡፡
የግንባታ ሥራዎች በጥናት ላይ ተሥርተው ሳይንሳዊ መንገድ ተከትለው መካሄድ እንዳለባቸውም አመላክተዋል።

በመሠረተ ልማት በኩል የሚስተዋሉ ስርቆቶችንና ችግሮችን ለመቅረፍ የኅብረተሰቡን ተሳትፎ ከፍ ማድረግ እንደሚገባም አንስተዋል።

በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር በ2013 በጀት ዓመት ለመሠረተ ልማት ግንባታዎች ከዓለም ባንክ የሚገኘውን የድጋፍ ገንዘብን ጨምሮ 526 ሚሊዮን ብር መበጀቱን ምክትል ከንቲባው አስታውቀዋል።

ዘጋቢ፡- ኪሩቤል ተሾመ

Previous articleየከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን የቅበላ ዝግጅት የሚያረጋግጡ 11 ተቆጣጣሪ ኮሚቴዎች ወደ ዩኒቨርሰቲዎች መላካቸውን ሚኒስቴሩ አስታወቀ።
Next articleየበረሃ አንበጣ መንጋን ለመከላከል በርጭት ላይ የነበረች ሄሊኮፕተር በወረባቦ ወረዳ ተከሰከሰች፡፡