
ባሕር ዳር፡ መስከረም 22/2013ዓ.ም (አብመድ) የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን የቅበላ ዝግጅት የሚያረጋግጡ 11 ተቆጣጣሪ ኮሚቴዎች የዩኒቨርሲቲዎችን ዝግጅት ለማረጋገጥ መሰማራቱን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።
ተቋማቱ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ከግምት ያስገባ ዝግጅት አድርገው በቀጣዩ ወር ተማሪዎችን የሚጠሩበትን ቀን ያሳውቃሉ ተብሏል።
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ደቻሳ ጉርሙ ለኢዜአ እንዳሉት ኮሚቴዎቹ ዩኒቨርሲቲዎቹ ያደረጉትን ዝግጅት ለመፈተሽ ትናንት ተሰማርተዋል።
ኢዜአ እንደዘገበው የተቋማቱ የኮሮናቫይረስን እየተከላከሉ የሚያስተምሩበትን ሁኔታ መፍጠራቸውን ኮሚቴዎቹ ካረጋገጡ በኋላ ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች የተማሪዎች ቅበላ ፕሮግራማቸውን ይፋ ያደርጋሉ።
የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ወደ ትምህርት የሚመለሱበት ቀን እስካሁን እንዳልተወሰነ የገለጹት ዳይሬክተሩ ከተቋማቱ የተማሪዎች ቅበላ ጋር ተያይዞ በማኅበራዊ ሚዲያና በሌሎች ምንጮች የሚሠራጨው መረጃ ስህተት እንደሆነ ገልጸዋል።
የኮሮናቫይረስ ቫይረስን ለመከላከልና የተማሪዎች መጨናነቅ እንዳይፈጠር በቅድሚያ የሚጠሩት ተመራቂ ተማሪዎች መሆናቸውንም አስረድተዋል።
ኮሚቴዎቹ በምልከታቸው ተቋማቱ ከመሠረተ ልማት አኳያ የተማሪዎች የመኝታ፣ የውኃ፣ የመፀዳጃና መሰል የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል የሚረዱ ዝግጅቶች ላይ ትኩረት እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።
በተጨማሪም ቫይረሱን መከላከያ መመሪያዎችን የሚያስተገብሩ የተቋማቱ መሪዎችና የሚመለከታቸው አካላት መሟላታቸውም ከግምት ውስጥ እንደሚገቡ ተመላክቷል።
ዩኒቨርስቲዎቹ ባላቸው አቅምና ዝግጁነት ልክ ተመራቂ ተማሪዎችን አስቀድመው ሌሎች ተማሪዎች የሚጠሩበት ሁኔታ እንደሚመቻች አቶ ደቻሳ አስረድተዋል።
“ይህም ተማሪዎቹ በመማሪያ ክፍልም ይሁን በሌሎች መገልገያ ቦታዎች እንዳይጨናነቁ ያደርጋል” ያሉት ዳይሬክተሩ በአንድ ማደሪያ ክፍል ውስጥ እስከ ሦስት ተማሪዎች እንደሚኖሩም ገልጸዋል።
ተቋማቱ ካለፉት ዓመታት በመማር ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሁኔታን ለመፍጠር ያደረጉት ዝግጅትም ከግምት ውስጥ እንደሚገባ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በአገሪቱ የኮሮናቫይረስ ከገባ በኋላ መዘጋታቸው ይታወቃል።