
ባሕር ዳር፡ መስከረም 22/2013ዓ.ም (አብመድ) የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል እና የገንዘብ ሚንስትር አህመድ ሺዴ ከሰሞኑ የ2020 የአፍሪካ ቢዝነስ ሥራ አመራር ሽልማት ማሸነፋቸው ይታወሳል፡፡
የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል የ2020 የአፍሪካ ቢዝነስ ሥራ አመራር ሽልማት አሸናፊ መሆናቸውን ተከትሎ ከአብመድ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
የአፍሪካ ቢዝነስ ሥራ አመራር ሽልማት በተቋም፣ በሀገርና በአህጉር ደረጃ በቢዝነስ አመራር በላቀ ደረጃ ውጤታማ ለሆኑ ጥቂት መሪዎች የሚበረከት የመልካም ተግባር የዕውቅና ሽልማት ነው፡፡ የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴም የዓመቱ ምርጥ የአፍሪካ ገንዘብ ሚኒስትር ሽልማትን ሲያሸንፉ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል ደግሞ የ2020 የአፍሪካ ቢዝነስ ሥራ አመራር ሽልማት አሸናፊ ሆነዋል፡፡
የንግድና ኢንዱስትሪ ዘርፉ መዋቅሩን ከፌዴራል እስከ ክልልና ከተማ አስተዳደር ድረስ በማነቃነቅ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተረጋጋ የግብይት ሥርዓት እንዲፈጠር በመሥራታቸው፣ ለኮሮናቫይረስ ተፅዕኖ የማይበገርና የሰከነ ንግድና ኢኮኖሚ መዘርጋት፣ ሥራ ዕድልን በማነቃቃት፣ አዳዲስ የልማት ሥራዎችን በማሳለጥ፣ የሀገር ውስጥ ንግድ እንዲያንሰራራ በማድረግና ሀገራዊ የኤክስፖርት ንግድ እንዲነቃቃ ለሰጡት የላቀ አመራር ማሳያ አድርጎ ተቋሙ ሸልሟቸዋል፡፡
በተለይ የአምራች ኢንዱስትሪዎች የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መከላከያ ግብዓቶችን እንዲያመርቱ በማድረግ አርአያነት ያለው አመራር በመስጠታቸው ይደርስ የነበረውን ጉዳት በጉልህ ማስቀረታቸው ተሸላሚ አድርጓቸዋል፡፡
ውል የተወሰደባቸው የግብራና የማኑፋክቸርቲንግ ምርቶች በልዩ ሁኔታ ወደ ውጭ እንዲላኩ በመደረጉ ኢትዮጵያ ብዙ ማትረፏና ለዚህም የእርሳቸው ብልህነት የተሞላበት አመራር ድርሻው ከፍ ያለ መሆኑም ተመላክቷል፡፡
“የአፍሪካ ትልቁ ችግር የሰከነ የአመራር ጥበብ አለማደግ፣ የቅንጅት አሠራር አለመኖርና ሊያሠሩ የሚችሉ ፖሊሲዎችን መፍጠር አለመቻል ነው” ያሉት ሚኒስትሩ ይህን መሻገር ከተቻለ አገርን መለወጥ እንደሚቻልም አስገንዝበዋል፡፡
ሽልማቱ የሁሉም ባለድርሻ አካላት የጋራ ጥረት ውጤትና በአጠቃላይ ለኢትዮጵያ የተሰጠ ዕውቅና መሆኑን በመግለጽም ምሥጋና አቅርበዋል፡፡
ዘጋቢ፦ ጋሻው ፋንታሁን -ከአዲስ አበባ