
በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር መስከረም 18/2013ዓ.ም ነፋስ እና በረዶ ቀላቅሎ የጣለ ዝናብ ከ80 ሄክታር በላይ የሚሆን የ211 የአርሶ አደሮች ማሳ ላይ ጉዳት መድረሱን አርሶ አደሮች ተናግረዋል፡፡ አቶ አያልነህ ፍሬው እንደነገሩን ከሁለት ሄክታር በላይ ማሳ ላይ የነበረ ሰብላቸው ሙሉ በሙሉ ጠፍቷል፡፡ ጉዳት ከደረሰባቸው ዋና ዋና ሰብሎች መካከልም በቆሎ፣ በርበሬ እና ዳጉሳ እንደሚገኙባቸው አርሶ አደሩ ተናግረዋል፡፡
የ2012/2013 የምርት ዘመን የክረምቱ ቆይታ እየተገባደደ በመሆኑ ሌላ ሰብል ዘርቶ ለማድረስም እንደሚቸገሩ ነው አርሶ አደሩ የተናገሩት፡፡ ለአፈር ማዳበሪያ እና ለሠራተኛ ከ15 ሺህ ብር በላይ ማውጣታቸውን የተናገሩት አርሶ አደሩ እገዛ እንዲያደረግላቸው ጠይቀዋል፡፡
የአየሁ ጓጉሳ ወረዳ የአደጋ መከላከል እና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ምላሽ ሰጪ ተወካይ ባለሙያ አልጋነህ መሠረት በበረዶ የተጎዳውን አካባቢ መረጃ እየሰበሰቡ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ የ211 አርሶ አደሮች በ80 ነጥብ 025 ሄክታር ማሳ ሰብል በበረዶው ጉዳት እንደደረሰበትም ተናግረዋል፡፡ ከተጎዳው ሰብል ዩሪያ በመጨመር፣ በመኮትኮት እና በማረም እንዲመለስ ለአርሶ አደሮች ምክርና ድጋፍ እየተደረገ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡
የአየሁ ጓጉሳ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ ነጋ ስዩም ጥናት ላይ ተመሥርቶ ለአርሶ አደሮቹ ብድር ሊመቻች እንደሚችል እና መድረስ የሚችሉ ሰብሎችን መልሰው እንዲዘሩ እንደሚደረግ አስታውቀዋል፡፡
ዘጋቢ፡- አዳሙ ሺባባው