አዲሱ የብር ኖት የዋጋ ግሽበትን እንዴት ሊታደገው ይችላል?

433

ባሕር ደር፡ መስከረም 21/2013ዓ.ም (አብመድ) የምጣኔ ሀብት ምሁራን የአንድ ሀገር የገበያ ሁኔታ የመንግሥት ጥንካሬ እና ድክመት መለኪያ ነው ይላሉ፡፡ የተረጋጋ ገበያ የጠንካራ መንግሥት የሥራ ውጤት ነው፡፡ ያልተረጋጋ ገበያ ደግሞ የደካማ መንግሥት ማሳያ ነው፡፡ በእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት መምህሩ ካሱ ኃይሉ በኢትዮጵያ አብዛኛው የገበያ ሥርዓት የሚዋዥቅ እና የአቅርቦት እጥረት ያለበት መሆኑን ያምናሉ፡፡ በኢትዮጵያ አዲሱ የብር ኖት ሥራ መጀመር ከባንክ ኢኮኖሚ ሲስተም ውጭ የነበረውን ገንዘብ በሥርዓት ሕጋዊ ሆኖ እንዲመራ እንደሚያደርገውም ተስፋ አድርገዋል፡፡

የአንድ ሀገር ብር በገበያ ውስጥ ሊበዛና በባንክ ሥርዓት ውስጥ ላይገባ የሚችልባቸው ምክንያቶች ገንዘብ ከባንክ ውጭ በመሆኑ እንደሌለ ተቆጥሮ አዲስ ሲታተም እና መንግሥት ዕዳን ለመክፈል ተጨማሪ ገንዘብ ወደ ገበያው ሲያስገባ ነው፡፡ መንግሥት ከፍተኛ የሆነ የውጭ ብድርን ለመመለስ አዲስ ገንዘብ ሲያትምና ወደገበያው ሲያስገባ የዋጋ ንረት ሊከተል ይችላል፡፡ ሌላው ደግሞ ኢኮኖሚው የሚፈልገውን ጥያቄ ለመመለስ እና ከአገልግሎት ውጭ የሆኑ ገንዘቦችን መልሶ ለመተካት እንደአዲስ ሲያትም መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ይህ ግን በአንድ ሀገር የገንዘብ ሕትመቱን ደረጃ ያልጠበቀ የባንክ ሲስተም ካለ አሁንም በርካታ ገንዘብ ውጪ ማደር እንዲጀምር በር ይከፍታል ብለዋል፡፡

በዚህ ጊዜ ሀገሪቷ ለኢንቨስተሮች የማበደር አቅም ታጣለች፣ ከመንግሥት ቁጥጥር ውጪ የሆነው ገንዘብ ያልተረጋጋ የገበያ ሥርዓት መፈልፈያም ይሆናል፡፡ ያልተረጋጋ ገበያ ደግሞ ጥቂት ባለጸጎች በብዙ ሥራ አጦች ይታጀባሉ፤ በጥቂት ገንዘብ የሚሠሩ ሠራተኞችም ይከበባሉ፡፡ይህ ከኢኮኖሚ ኢ-ፍትሐዊነት በተጨማሪ ያልተረጋጋ መንግሥት መገለጫ ነው፡፡ ምሁሩ እንደተናገሩት በባንክ ሥርዓት የሚያልፍ ገንዘብ መኖር የባንኮችን የማበደር አቅም ያሳድጋል፤ የተበደሩ አልሚዎችም ለበርካቶች የሥራ ዕድል ምንጭ እየሆኑ እንዲሄዱ ያደርጋል፡፡

የአንድ ሀገር ምጣኔ ሀብት ጤናማነት ከሚመዘንባቸው መሠረታዊ መስፈርቶች ውስጥ ዋነኛው የገበያ ሥርዓቱ ያለበት ሁኔታ ነው፡፡ ጤናማ ምጣኔ ሀብት የዝቅተኛ የዋጋ ግሽበት መድረክ፣ ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት ያለው፣ ዝቅተኛ የሥራ ፈላጊዎች ቁጥር ያለው እና ሀገሪቷ ለዓለማቀፍ ማኅበረስብ የምትከፍለውና የምትቀበለውን ብድር የተመጣጠነ ሲሆን ነው፡፡ ይህ ደግሞ የፍትሐዊ ሀብት ክፍፍል ማሳያ ነው፤ የቀጣይ ትውልድ ፍላጎት ላይ የተመሠረተ የኢኮኖሚ መሠረትም ነው፤ እነዚህ ደግሞ የጠንካራ መንግሥት መገለጫ ናቸው፡፡

በኢትዮጵያ በከተሞች አንድ እንቁላል 6 ብር፣ አንድ ኪሎ ስጋ 400 ብር ፣ አንድ ኪሎ ጤፍ በአማካኝ 40 ብር፣ አንድ ኪሎ ብርቱካን በአማካኝ 60 ብር የሚሸጥባቸው ከተሞች ሲፈጠሩ የተወደዱ ጥሬ ዕቃዎችን አብሮ በማስወደድ ሥራ ፈላጊ ወገኖች ሥራ ካላቸው ይበዛሉ፡፡ ጠንካራ መንግሥት በእነዚህ ዘርፎች ላይ ሥራ ፈላጊዎችን አደራጅቶ በማሰማራት ገበያውን ያረጋጋል፡፡ ጠንካራ መንግሥት የኅብረት ሥራ ማኅበራትን አቅም ከማገዝ በተጨማሪ በቀጣይ ሊኖር የሚችሉ ዑደቶችን በመተንበይ አቅርቦቶችን ለዋጋ ንረት ምክንያት እንዳይሆኑ ይሠራል፡፡ ደካማ መንግሥት ደግሞ ጥሬ ዕቃዎች እጥረት እየገጠማቸው፣ ዋጋቸው እየናረ፣ ደመወዝ ቢጨምርም፣ ደመወዙን የጥሬ ዕቃ ግዥ እየወሰዱበት በ40 እና 50 ዓመታት ውስጥ የራሳቸው መኖሪያ ቤት የሌላቸው የቤተሰብ መሪዎች መፈጠር እንዲችሉ ያደርጋል፡፡ የሥራ አጥነት ቁጥር መብዛት እና ተቀጣሪዎችም የሚከፈላቸው ዝቅተኛ ገንዘብ መሆንም ያልተረጋጋ መንግሥትን ሊያስከትል ይችላል፡፡

በገበያ ላይ ደካማ መንግሥት የሚለካው በገበያው ውስጥ ባለው ጣልቃ ገብነት መጠን እና ገበያው እንዳይወድቅ ባደረገው ጥረት እና በተሳካለት ልክ ነው፤ ምክንያቱም መንግሥት ገበያውን በረጅሙ ለራሱ፣ ለገበያው እና ለግል ሴክተሩ በመስጠት ሌሎች መሠረታዊ ሥራዎች ላይ ባለው ተሳትፎ ይለካል፡፡ የምጣኔ ሀብት ምሁራን በዓለም ላይ ሁለት ዓይነት የገበያ መውደቅ መኖሩን ያመላክታሉ፡፡ አንደኛው ኢኮኖሚው ምንም ዓይነት ምርት እና አገልግሎት ለገበያው ማቅረብ ሳይችል ሲቀር ሲሆን ሁለተኛው ገበያው ቢኖርም ከፍላጎት አንጻር በቂ ያልሆነ ምርት በተጋነነ ዋጋ ሲያቀርብ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ስላለው የገበያ ሁኔታ ግን በአብዛኛው ወደ ሁለተኛው (Complete market failure) የሚያደላ እንደሆነ ያምናሉ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ተፈላጊውን ምርት በሀገር ውስጥ አለመመረት እና ከውጭ ሀገር ተገዝተው ማስገባት ላይም ውስንነት መኖር እንደሆነ ምሁሩ አስረድተዋል፡፡ ይህ የዋጋ ንረትን የሚጠራ አሠራር ነው፡፡ የዋጋ ንረት መገለጫው ተከታታይ የቁሳቁስም ሆነ የአገልግሎት ዋጋ በመጨመር ምክንያት የሰዎች የመግዛት አቅም መዳከም ነው፡፡ ይህም የኑሮ ውድነት ጣሪያ የመንካት ሁኔታ ነው፡፡

እንደምሁሩ ማብራሪያ በኢትዮጵያ የዋጋ ግሽበት በጽንስ ሐሳብ ደረጃ ዕድገት ሲመጣ የሰዎች የመጠቀም ፍላጎት ስሚበዛ የሚመጣ መሆኑን የሚገልጹ አሉ፤ የዕቃዎች አቅርቦት እጥረት መኖርን የሚያነሱም አሉ፡፡ በኢትዮጵያ ለዋጋ ግሽበት ከፍተኛ የሆነ የምግብ እህሎች እጥረት መኖር አንዱ ምክንያት ነው፡፡ የሕዝብ ቁጥር እያደገ ቢሆንም የግብርናው አለመዘመንና ምርታማነቱ ከሕዝቡ ቁጥር ጋር አለመጣጣም ዋጋ እየጨመረ እንዲመጣ አድርጎል የሚል ዕይታ አላቸው፡፡

አዲሱን የገንዘብ ኖትም በባንክ ሲስተም መምራት የገንዘብ አያያዝን ከማሻሻል ውጭ አቅርቦትን ሊያፋጥን ስለማይችል ተጓዳኝ የአቅርቦት ማዘመን ሥራዎች ካልተሠሩ ብቻውን መፍትሔ ሊሆን እንደማይችል አመላክተዋል፡፡ በገበያ ፍላጎቶች ላይ የተመሠረቱ የሥራ ዕድሎች መፍጠርም ዓይነተኛ የመፍትሔ አካል ነው፡፡ መምህር ካሱ ኢኮኖሚውን የሚያዳክም ከሲስተም ውጭ የሆነ ገንዘብ እንዳይፈጠርም የቴሌኮም አገልግሎት ወሳኝ እንደሆነ አመላክተዋል፡፡ ማዕከላዊ ባንክ የሚቆጣጠረው ተደራሽነታቸውን ያሰፉ እና አንድ ወጥ የሆነ ሲስተም በመፍጠር ሕዝቡ በቀላሉ የሚገዛበትና የሚሸጥበትን ዕድል በቴሌኮ በኩል መፍጠር እንደሚገባም መክረዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ግርማ ተጫነ

Previous articleየብሔራዊ ፀጥታ አስተባባሪ ኮሚቴ በወቅታዊ የሰላም ሁኔታ ላይ መግለጫ ሰጥቷል፤ የመግለጫው ሙሉ ሐሳብ ቀጥሎ ቀርቧል።
Next articleለታላቁ ሕዳሴ ግድብ ዘንድሮ ከ1 ነጥበ 2 ቢሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ መታቀዱ ተገለፀ።