የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ የጋፋት ኢንዱስትሪ መንደርን ለማልማት እና ታሪኩን በሰፊው ለማስተዋወቅ እየሠራ መሆኑን አስታወቀ፡፡

330

ባሕር ዳር፡ መስከረም 22/2013ዓ.ም (አብመድ) የደቡብ ጎንደር ዞን ባህል እና ቱሪዝም መምሪያ “ቱሪዝም ለገጠር ልማት” በሚል መሪ ሐሳብ እየተከበረ ያለውን የቱሪዝም ቀን አስመልክቶ በዞኑ የሚገኙ የቱሪስት መዳረሻዎችን አስጎብኝቷል፡፡ መምሪያው በዞኑ ያሉ የቱሪስት መዳረሻዎችን በማልማት ከዘርፉ ተጠቃሚ ለመሆን እንደሚሠራም አስታውቋል፡፡

በዓለም ለ44ኛ፣ በኢትዮጵያ ለ33ኛ እና በክልሉ ለ28ኛ ጊዜ የ2013 ዓ.ም የዓለም ቱሪዝም ቀን “ቱሪዝም ለገጠር ልማት” በሚል መሪ ሐሳብ ተከብሯል፡፡ የደቡብ ጎንደር ዞን ባህል እና ቱሪዝም መምሪያም በዓሉን የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎችን በመጎብኘት ማክበሩን አስታውቋል፡፡ በጉብኝቱ የዞኑ የባህል እና ቱሪዝም ባለሙያዎች፣ የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ምሁራን እና ሌሎች ባለድርሻ እና አጋር አካላት ተሳትፈዋል፡፡

ከክርስቶስ ሰምራ እስከ ደብረ እንቁ፣ ከማኅደረ ማሪያም እስከ ግንብ ጊዮርጊስ፣ ከቤተልሔም እስከ ዙር አምባ ማሪያም፣ ከፈሳስ ላልይበላ እስከ ቆማ ፋሲለ ደስ፣ ከብሯደጌ አስከ ጣራ ገዳም፣ ከአምስትያ እስከ ጉና በዞኑ ካሉ የቱሪስት መዳረሻዎች ብዙ ያልተጎበኙ የዞኑ የመስህብ ሀብቶች ናቸው፡፡ “ዞኑ የበርካታ ጥንታዊ እና ታሪካዊ ቅርሶች ባለቤት ነው” ያሉት የዞኑ ባህል እና ቱሪዝም መምሪያ የቅርስ ጥበቃና ቱሪዝም ልማት ቡድን መሪ ገደፋው ወርቁ ናቸው፡፡ በመካከለኛው ዘመን በአፄ ሰርፀ ድንግል የተመሠረተቸውን ጥንታዊ እና ታሪካዊ ይዘት ያላትን ማኅደረ ማርያም እና ግንብ ጊዮርጊስ ተጎብኝተዋል፡፡ ማኅደረ ማሪያም በፋርጣ ወረዳ ስትገኝ ግንብ ጊዮርጊስ ደግሞ በአንዳቤት ወረዳ ይገኛሉ፡፡ መምሪያው በዞኑ ያሉ የቱሪስት መዳረሻዎችን በማልማት ከዘርፉ ተጠቃሚ ለመሆን እየሠራ መሆኑንም አቶ ገደፋው ጠቁመዋል፡፡

በደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ የቱሪዝም ልማት ትምህርት ክፍል ኃላፊ ዳኛቸው ነጋ ዞኑ የበርካታ ቅርሶች ባለቤት መሆኑን አውስተው፤ ነገር ግን በተገቢው መንገድ ለቀሪው ዓለም እንዳልተዋወቀም ጠቅሰዋል፡፡ የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ የጋፋት ኢንዱስትሪ መንደርን ለማልማት እና ታሪኩን በሰፊው ለማስተዋወቅ ከሌሎች ዩኒቨርሲቲዎችና ከሚመለከታቸው አጋር አካላት ጋር እየሠራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው መዳረሻዎች ድጋፍ እና ጥገና ለሚያስፈልጋቸው ቅርሶች በዕውቀት ላይ ተመሥርቶ ጥገና ለማድረግ በቅርበት እየተሠራ መሆኑንም አቶ ዳኛቸው ጠቁመዋል፡፡

ዘጋቢ፡-ታዘብ አራጋው

Previous articleአመልድ ጆንስ ሪግ ዋሽ ፕሮጀክት የ4 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ፡፡
Next articleየብሔራዊ ፀጥታ አስተባባሪ ኮሚቴ በወቅታዊ የሰላም ሁኔታ ላይ መግለጫ ሰጥቷል፤ የመግለጫው ሙሉ ሐሳብ ቀጥሎ ቀርቧል።