ሕዝባዊ ተሳትፎ ያላቸው የስፖርት ማዘውተሪያ ማዕከላትን ማስፋፋት እንደሚገባ የአማራ ክልል ስፖርት ፌዴሬሽኖች አስታወቁ፡፡

276

ባሕር ዳር፡ መስከረም 22/2013ዓ.ም (አብመድ) የአማራ ክልል ስፖርት ፌዴሬሽኖች እና ኮሚቴዎች ጠቅላላ ጉባኤ ትናንት ሲካሄድ ሕዝባዊ ተሳትፎ ያላቸው የስፖርት ማዘውተሪያ ማዕከላትን መገንባት እና ሕጋዊ የይዞታ ማረጋገጫ መቀበል ትኩረት የሚሰጣቸው ተግባራት መሆናቸውን አመላክተዋል፡፡
16 የክልሉ የስፖርት ፌዴሬሽኖች በቀጣይ አራት ዓመታት የሚመሩ ፕሬዝዳንቶች እና የሥራ አስፈጻሚዎችን ሲመረጡ የ10 ዓመታት እቅዳቸውንም ገምግመዋል፡፡

የግምገማው ተሳታፊዎች በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች ያሉ የስፖርት ክህሎቶች ላይ መሠረት ያደረገ ሕዝባዊ ተሳትፎን ያረጋገጠ ዘርፍ መገንባት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ ሁሉን አቀፍ የስፖርት መለማመጃ ሜዳዎችን መሥራት አሁንም ከፊት የሚመጣ ተግባር መሆኑንም ተነጋግረዋል፡፡ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና ከባለሀብቶች ጋር አብሮ መሥራት እንደሚገባም ተመላክቷል፡፡

‘‘በሕገ ወጥ ግንባታ ምክንያት የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎች እየጠፉ ናቸው’’ ያሉት ተሳታፊዎቹ በከተሞች በቂ የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎች ባለመኖራቸው ዜጎች ጤናቸውን እንዲያስጠብቁና ክህሎታቸውን እንዲጠቀሙ እያደረገ አለመሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

የስፖርታዊ ጨዋነት፣ የዳኝነት እና የአስልጣኞች ስልጠና መስጠት እንደሚገባ ያመላከቱት ተሳታፊዎቹ የስፖርት መዋቅሩን ለውድድር ብቻ በመፈለግ የሚስተዋለው ችግር ከዘርፉ ኢንቨስትመንት ተጠቃሚ መሆን እንዳይቻል ማድረጉንም አመላክተዋል፡፡

የክልሉ ስፖርት ማኅበራት ዕውቅናና ድጋፍ ዳይሬክተር ሙሉጌታ ሉሌ ‘‘ብቃት ያላቸው ዳኞች አሉን፤ ነገር ግን ተጨማሪ ዳኞች እንዲፈሩ ወረዳዎች እና ዞኖች የመጀመሪያ ደረጃ ስልጠናዎች መስጠት ላይ ክፍተት አለ’’ ሲሉ ተናግረዋል፡፡ በቀጣይ ይህንን ኃላፊነታቸውን መዋጣት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የክልሉ ስፖርት እንዲያድግ የተጀመሩ ትልልቅ የስፖርት ማዕከላት እንዲጠናቀቁ እና የስፖርት ማዘውተሪያ እጥረት ያለባቸው አካባቢዎችን ችግር ለመፍታት እንደሚሠሩም ተናግረዋል፡፡ ስፖርቶች ሕዝባዊ መሠረት እንዲኖራቸው አሳታፊ ማድረግ እና ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር በስልጠና እና ቁሳቁስ ድጋፍ እንዲያደርጉ የተጀመሩ ጥረቶችን ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባቸው አሳሰበዋል፡፡

የስፖርት ሙያተኞች ወደ መሪነት እንዲመጡ ብቃታቸውን ማሳደግ እንደሚገባና በሙያተኞች ባለመመራታቸው የተፈጠሩ ክፍተቶችንም በመተጋገዝ ማብቃት እንደሚገባ አቶ ሙሉጌታ ተናግረዋል፡፡

በአማራ ክልል ከ22 በላይ የስፖርት ዓይነቶች በፌዴሬሽኖች ታቅፈዋል፤ ይሁን እንጂ የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታ እጥረት ከፍተኛ ችግር ነው፡፡ በከተሞች ሰዎች መንገድ ዘግተው የሚጫወቱበት ጊዜም ብዙ ነው፡፡ ይህም በዘርፉ ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት እንቅፋት ከመሆኑ በላይ ጤናማ ማኅበረስብ ለመፍጠር የታሰበውን እቅድ እንቅፋት ሆኖበታል፡፡

ዘጋቢ፡- ግርማ ተጫነ

Previous articleየቲሊሊ ከተማና አካባቢው ኅብረተሰብ ኪሊ መስክ ትምህርት ቤትን በአዲስ ገነቡ፡፡
Next articleአመልድ ጆንስ ሪግ ዋሽ ፕሮጀክት የ4 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ፡፡