
ባሕር ዳር፡ መስከረም 22/2013ዓ.ም (አብመድ) የአማራ ልማት ማኅበር (አልማ) የክልሉን ሕዝብ ሁለንተናዊ ችግሮች ለመቅረፍ የሚደረገውን ጥረት በማገዝ በኩል ዓመታትን የተሻገረ ሥራን አባላቱን እና ደጋፊዎችን በማስተባበር እየሠራ ይገኛል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ ቁጥር ያለው የአማራ ተወላጅ ቢኖርም የአልማ አባል የሆነው እና ልማቱን የሚደግፈው ቁጥር ግን አነስተኛ ነው፡፡
በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ቁጥሩ ከፍ ያለ የአማራ ተወላጅ ቢኖርም በአባልነት ተመዝግቦ ያለው ከ3 ሺህ 600 አይበልጥም፡፡ ይህን ለማሳደግና የአልማን እንቅስቃሴ ደጋፊ ለማድረግ ሥራዎች እየተሠሩ ነው፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳር የከንቲባ አደረጃጀት ዘርፍ አማካሪና የአዲስ አበባ አልማ ኮሚቴ ሥራ አስፈጻሚ አባል አቶ ተተካ በቀለ ላለፉት ሁለት አስርተ ዓመታት የክልሉን ልማት በማገዝ መንግሥት እጅ ሲያጥረው በመደገፍና የደከሙ ጉልበቶችን ሲደግፍ መቆየቱን ገልፀዋል። አልማ የክልሉን ሕዝብ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ሲያግዝ መቆየቱንም ተናግረዋል፡፡
አልማ በ2013 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ያለውን አባልና ደጋፊ በማስተባበር ሁለት ዋና ዋና ጉዳዮችን ለማሳካት እየሠራ መሆኑንም አቶ ተተካ ተናግረዋል፡፡ የሕዝቡን የመበልጸግ ፋላጎት ለማሳካት እና አማራ እንደ ሕዝብ ችግር ሲገጥመው የፖለቲካ አስተሳሳብ ሳይገድበው የአማራን ሕዝብ ሁለንተናዊ አቅም ለማሰባሰብ አልማ ጥላ መሆኑን በመግለጽም ሁሉም ከፊት ሆኖ መምራት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የብልጽና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊና የክፍለ ከተማው የአልማ ኮሚቴ ሰብሳቢ እርጋታው ብዙአየሁ አልማ የአማራን ሕዝብ ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ የሚሠራውን ሥራ ለመደገፍ አባላቱን በማስተባበር እየተሠራ ቢሆንም በክፍለ ከተማው ካለው ከፍተኛ የአማራ ተወላጅ ቁጥር አንጻር ሲታይ በአልማ ስር ተመዝግቦ እየደገፈ ያለው ከ3 ሺህ 600 መቶ የማይበልጥ መሆኑን አመልክተዋል። ይህን ለመቀየር በክፍለ ከተማው በዚህ ዓመት ብቻ አዲስ ከ25 ሺህ በላይ አባላትን ለማቀፍ እንቅስቃሴ መጀመሩን አስታውቀዋል። ለአማራ ባህል ማዕከል ግንባታ በ2012ዓ.ም በክፍለ ከተማ ደረጃ የተሰጠውን የ5 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር ድጋፍ በማሳደግ በዚህ ዓመት 10 ሚሊዮን ብር ሰብስቦ ድጋፍ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡
ሀብትና አስተሳሰብን ማሰባሰብና ስለአማራ ሕዝብ ሁለንተናዊ ግንዛቤ ማሳደግ ላይ በትኩረት እንደሚሠሩም አቶ እርጋታው ጠቁመዋል። የየትኛውም ብሔር ተወላጅ አልማን ለመደገፍ በአባልነት እንዲመዘገብ ለማድረግ በትኩረት የሚሠሩ ሥራዎች መኖራቸውንም ለአብመድ ተናግረዋል፡፡
ክፍለ ከተማው ዓመታዊ ጉባኤውን አባለቱ፣ ደጋፊዎቹ እና መሪዎቹ በተገኙበት አካሂዷል። በዚህም በ2012ዓ.ም የአልማ አፈጻጸም እና የ2013 ቁልፍ ሥራዎች ዙሪያ መክሯል፡፡ አሁን ያለውን የአባላት ቁጥር ይበልጥ ለማሳደግ የንቅናቄ እና ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ ተጠናክሮ ሊሠራ እንደሚገባም ተሳታፊዎች አሳስበዋል፡፡
ዘጋቢ፦ ጋሻው ፈንታሁን -ከአዲስ አበባ