
ባሕር ዳር፡ መስከረም 21/2013ዓ.ም (አብመድ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ሽታዬ ምናለን ጨምሮ የክልሉ የሥራ ኃላፊዎች በፎገራ ወረዳ ጣና ሞልቶ በመጥለቅለቁ ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎችን ሁኔታ ተመልክተዋል፡፡ በምክር ቤቱ የሴቶች ኮከስ በኦሮሚያ ክልል ተፈጥሮ በነበረው ሰው ሠራሽ አደጋ ችግር ላጋጠማቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ገንዘብ በማሰባሰብ ድጋፍ ማድረጉን ምክትል አፈጉባኤዋ ወይዘሮ ሽታየ ምናለ ገልጸዋል፡፡
በዚህ ሳምንትም በአፋር፣ ኦሮሚያ፣ ሶማሌ፣ ጋምቤላ እና አማራ ክልሎች በተለያዩ አደጋዎች ጉዳት ለደረሰባቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ በማድርግ ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡ በፎገራ ወረዳ ጣና ሞልቶ በመጥለቅለቁ ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎችንም ከቦታው ተገኝተው ተመልክተዋል፡፡
ድጋፉ መልካም ቢሆንም መንግሥት በዘላቂነት የሚቋቋሙበትን መንገድ እንዲያመቻችላቸው ተፈናቃይ አርሶ አደሮች ጠይቀዋል፡፡ መንግሥት በአጭር ጊዜ ሊደርሱ የሚችሉ የሰብል ዘሮችን ሊያቀርብላቸው እንደሚገባ ነው አርሶ አደሮቹ የጠየቁት፡፡ በጎርፉ የንጹሕ መጠጥ ውኃ ተቋማት ጉዳት ስለደረሰባቸው ንጽሕናው ያልተጠበቀ ውኃ እየተጠቀሙ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡
የአማራ ክልል አደጋ መከላከል ምግብ ዋስትና እና ልዩ ድጋፍ የሚሹ አካባቢዎች ማስተባበሪያ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘላለም ልጃለም ተጎጅዎችን በቋሚነት እስኪቋቋሙ ድጋፉ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡ ጣና ሐይቅ ወደተጥሯዊ ይዞታው በሚመለስበት ወቅት ለተፈናቃዮች የሚውል 8 ሺህ ኩንታል ዘር እንደሚያስፈልግ ኮሚሽነር ዘላለም ተናረዋል፡፡ በመሆኑም አርሶ አደሮች በአጭር ጊዜ አምርተው ራሳቸውን እንዲችሉ ኮሚሽኑ የዘር ግዥ እንዲፈጸም ከልማት ድርጅቶች እና መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር እየተነጋገሩ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
በሌሎች አካባቢዎችም በበረዶ እና በመሬት መንሸራተት ንብረታቸው ለወደመባቸው በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚኖሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች መንግሥት ድጋፍ እያደረገ መሆኑን አቶ ዘላለም ገልጸዋል፡፡ እንደ ኮሚሽነሩ መረጃ በክልሉ ከፍተኛ በሆነ የዝናብ መጨመር ምክንያት በተፈጠረ ጎርፍ፣ በበረዶ እና የመሬት መንሸራተት ምክንያት ከ20 ሺህ በላይ ሰዎች ተፈናቅለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሰራ