
ባሕር ዳር፡ መስከረም 21/2013ዓ.ም (አብመድ) በአዲስ አበባ ልደታ ክፍለ ከተማ ከ35 ሺህ ብር በላይ ነባሩ ባለሃምሳ ሐሰተኛ የብር ኖት ከነተጠርጣሪው ተይዞ ምርመራ እየተጣራ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ገለፀ፡፡
የአዲስ አበባ እና የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን አባላት ከጥርጣሬ በመነሳት በአንድ ግለሰብ ላይ ባደረጉት ድንገተኛ ፍተሻ በእጅ ቦርሳው ውስጥ 35 ሺህ 50 የቀድሞውን ባለሃምሳ ሐሰተኛ የብር ኖት ከአንድ የንግድ ባንክ ቅርንጫፍ ቲተር ጋር ከእነተጠርጣሪው በቁጥጥር ስር አውለዋል ብሏል ኮሚሽኑ፡፡
የልደታ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የልዩ ልዩ ወንጀሎች መርማሪ ምክትል ሳጅን ንጉሴ ማናዬ ኅብረተሰቡ ግብይት በሚፈጽምበት ወቅት በሐሰተኛ የብር ኖቶች የማታለል ወንጀል እንዳይፈጸምበት መለያዎቹን በጥንቃቄ በመመልከት እንዲገበያይ እና አጠራጣሪ ነገሮች ሲያጋጥሙ ለፖሊስ ጥቆማ እንዲሰጥ ማሳሰባቸውን ኢብኮ ዘግቧል፡፡