
ባሕር ዳር፡ መስከረም 21/2013ዓ.ም (አብመድ) በአምልኮ ቦታዎች የሚገኙ ዛፎች ቅዱሳን አባቶች እና እናቶች በቅድስና የጸለዩባቸው፣ በሥራቸው አፅም ያረፈባቸው በመሆናችው ትውልድ በጥንቃቄ ሊንከባከባቸው እንደሚገባ ተገልጿል፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክ ተዋህዶ አብያተ ክርስቲያናት አካባቢ ባለ የተፈጥሮ ደን እና ብዝኃ ሕይወት ያለበትን ደረጃና ፈተናዎች በተመለከተ ዛሬ በባሕር ዳር ጥናታዊ ጽሑፍ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡ ጥናታዊ ጽሑፉን ያቀረቡት የአማራ መልሶ ማቋቋም ድርጅት (አመልድ) ዋና ዳይሬክተርና የብዝኃ ሕይወት ተመራማሪ ዓለማየሁ ዋሴ (ዶክተር) ዜጎች በአምልኮ ቦታዎች የሚገኙ ደኖችን ኃላፊነት በተሞላ መልኩ መጠበቅ እና ለቀጣይ ትውልድ ማስተላለፍ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
በኢትዮጵያ ጥናቱ ከተደረገባቸው 50 ሺህ በላይ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ 35 ሺህ የሚሆኑት ከግማሽ ሄክታር በላይ የተፈጥሮ ደኖችን መያዛቸውን ዶክተር ዓለማየሁ ዋሴ ተናግረዋል፡፡ እነዚህ ደኖች ቅዱሳን የሚጸልዩባቸው አባቶች ለእርቅ፣ ለሽምግልና የሚቀመጡባቸው፣ አጽመ ቅዱሳን የሚያርፍባቸው መሆናቸው ተገልጿል፤ በርካታ አዕዋፋት እና አራዊት የሚገኙበት የሕይወት መስተጋብር እንዳይጠፋ የሚያደርጉ በመሆናቸው ልዩ ጥበቃ እንደሚያስፈልጋቸው ጥናት አቅራቢው ገልጸዋል፡፡
ባለፉት መቶ ዓመታት በተፈጥሮ ደን ላይ ለተለያዩ ምክንያቶች ጭፍጨፋ እንደተደረገና ሽፋኑ ከ40 በመቶ ወደ ሁለት በመቶ ዝቅ ማለቱን በጥናት መረጋገጡን ዶክተር ዓለማየሁ ዋሴ ተናግረዋል፡፡ አሁን የሚተከሉ ችግኞችም በቀላሉ ነባሮችን ስለማይተኩ ለነባር የተፈጥሮ ደኖች እንክብካቤ እንደሚያስፈልግ አመላክተዋል፡፡
“ቤተ ክርስቲያን የገነት ምሳሌ ናት፤ ማንኛውም የቤተ ክርስቲያን ይዞታ ገነት መምሰል አለበት” ብለዋል ጥናት አቅራቢው፡፡ “በቤተ ክርስቲያን አካባቢ የሚገኙ ደኖችም ለእኛ ተፈጥረው እኛ እንድናጠፋቸው አልተፈቀደም፤ እናም ሁሉም ዜጋ ኃላፊነቱን መወጣት አለበት” ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የልማት እና ክርስቲያናዊው ተራድኦ ኮሚሽነር ይልቃል ሽፈራው እንዳሉት ኮሚሽኙ ከተመሠረተ 1964 ዓ.ም ጀምሮ በ19 አብያተ ክርስቲያናት አካባቢ የተፈጥሮ ደን እንዲጠበቅ እና የተራቆተው አካባቢ በደን እንዲሽፈን ተደርጓል፡፡ አሁን ያለው ጥቂት የደን ሽፋንም በአብያተ ክርስቲያናት አካባቢ መሆኑን ኮሚሽነሩ ጠቅሰዋል፤ በቀጣይ ተደራሽነትን በማስፋት፣ ጥበቃ ማድረግ፣ ግንዛቤ መፍጠር ሥራ ተጠናክሮ መሥራት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ዓምደሃይማኖት ቆሞስ አባ ፅጌድንግል ፈንታሁን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ከጥንት ጀምሮ ሀገር በቀል ደኖችን ጠብቃ ያቆየች መሆኗን ተናግረዋል። በአስተምህሮ ሕግም ኅብረተሰቡ ደኖችን እንዲጠብቅ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ኅብረተሰቡ ደን የማልማት ልምዱን በመልካም ተሞክሮነት ጠቅሰዋል፡፡ በብሔረሰብ አስተዳደሩ አብያተ ክርስትያናት አካባቢዎች በጽድ፣ ወይራ፣ ቀርከሃ እና በተለያዩ ሀገር በቀል ዛፎች የተሸፈኑ መሆናቸውን ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡ ሌሎችም ተሞክሮውን መውሰድ እንዳለባቸውም አንስተዋል፡፡
ከምዕራብ ጎጃም ዞን የእስልምና ምክር ቤት የተገኙት የውይይቱ ተሳታፊ ሻምበል ሙስጠፋ ሙሉዓለም በእስልምና ተቋማትንና የመቃብር ቦታዎችን በአረንጓዴ ለመሸፈን እየተሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ “ያለ ደን ሕይወት የለም” ያሉት ሻምበል ሙስጠፋ የለማ አካባቢን ለትውልድ ለማስረከብ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በእስልምና ሃይማኖት አስተምህሮም አንድ ዛፍ መትከል አንድ ልጅ ወልዶ እንደማሳደግ የሚቆጠር መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ነብዩ ሙሐመድም ከመነሻቸው ጀምሮ አረንጓዴ እና ልምላሜ ያለበትን ቦታ ይፈልጉ ስለነበር ዛፍ መቁረጥ በእስልምና ሃይማኖት ዘንድ የተከለከለ እንደሆነ ማስተማራቸውን ገልጸዋል፡፡
ዘጋቢ፡- አዳሙ ሽባባው