
መስከረም 23 እና 24 የሚከበረውን የኢሬቻ በዓል ለመረበሽ የተዘጋጁ 503 ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄኔራል ኮማንደር አራርሳ መርዳሳ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደገለፁት የኢሬቻ በዓል ላይ የሚሳተፉ የበዓሉ ታዳሚዎች በሰላም ወጥተው እንዲገቡ ኮሚሽኑ በጥብቅ እየሠራ ነው።
የግል ፍላጎታቸውን ለማሳካት በተለያየ አቅጣጫ እየተንቀሳቀሱ ያሉ ኃይሎች እንዳሉና ኮሚሽኑም እንደደረሰባቸው የገለፁት ኮማንደሩ እስካሁን ድረስ 503 ሰዎች፣ 14 ክላሽ፣ 26 ቦምብ እና 103 ሽጉጦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተናግረዋል፡፡
ከኦሮሚያ ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ያገኘነውን መረጃ ዋቢ አድርጎ ኢፕድ እንደዘገበው የኢሬቻ በዓል በኮሮናቫይረስ ምክንያት እንደ ከዚህ ቀደሙ በርከት ባለ ሰው የማይከበር ሲሆን በገዳ አባቶች የተላለፈውን ውሳኔን ኅብረተሰቡ ሥራ ላይ ማዋል እንዳለበትም ኮማንደር አራርሳ ተናግረዋል፡፡
ኅብረተሰቡ ከፀጥታ ኃይሉ ጋር በመሆን ከህወሓት እና ከሸኔ የተሰጣቸውን ግዳጅ በመውሰድና ኦሮሚያን የጦርነት አውድማ ለማድረግ እየተንቀሳቀሱ ያሉ ኃይሎችን በማጋለጥ በዓሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የስልጣን ጥም ያላቸው አካላት “ከመስከረም 25 በኋላ መንግሥት የለም” እያሉ ኅብረተሰቡን ለማወክ የሚፈልጉ አካላት በምንም ሁኔታ እንደማይሳካላቸው ኮማንደር አራርሳ ተናግረዋል፡፡
የኦሮሚያ ፖሊስ የሕዝቡን ሰላም የሚያውኩትን በመከታተል ሕግ ለማስከበር በቁርጠኝነት መዘጋጀቱንም ኮሚሽነር ጄኔራሉ አስታውቀዋል፡፡