በሀገር አቀፍ ደረጃ የመምህራንን ቀን ለማክበር መዘጋጀቱን ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

807

የትምህርት ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ መምህራ ማኅበር በጋራ በመሆን የመምህራን ቀን አከባበር ላይ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ገረመው ሁሉቃ (ዶክተር) መምህራን ትውልድን በመቅረፅ ውስጥ ትልቅ ሚና ስላላቸው ለመምህራን አስፈላጊውን ዕውቅና እና ክብር መስጠት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡ መንግሥትም ከዘንድሮ ጀምሮ በሀገር አቀፍ ደረጃ የመምህራን ቀን እንዲከበር መወሰኑንም ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡

የዘንድሮውን የመምህራን ቀን ለየት የሚያደርገው ከዚህ ቀደም በመምህራን ማኅበር የሚከበረውን ይህን ቀን መንግሥት ኃላፊነቱን ወስዶ ለማክበር በመዘጋጀቱ መሆኑም ተገልጿል፡፡

ቀኑንም መምህራንን በማክበር፣ በማሰብ እንዲሁም የተለያዩ ጥናታዊ ጽሑፎችን በማቅረብ እና የፓናል ውይይት በማድረግ ታስቦ እንደሚውል ተነግሯል፡፡

የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር ፕሬዝዳንት ዮሐንስ በንቲ (ዶክተር) በበኩላቸው ቀኑን ከማክበር ባሻገር ቀድሞ የነበረውን የመምህራንን ክብር እና ጥያቄ ለመመለስ ይሠራል ብለዋል፡፡

የመምህራን ቀኑም ከመስከረም 20 ጀምሮ ለአንድ ወር ያህል ወጥነት ባለው መልኩ ከትምህርት ቤት እስከ ሀገር አቀፍ ደረጃ የሚከበር መሆኑ ተመላክቷል፡፡

የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር ከ600 ሺህ በላይ አባላተ መምህራን እንዳሉት የትምህርት ሚኒስቴር በማኅበራዊ ገጹ አስታውቋል፡፡

Previous articleየባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ባለፈው በጀት ዓመት ከ38 ሺህ በላይ የተለያዩ ሕገ ወጥ ግንባታዎችን ማፍረሱን አስታወቀ።
Next articleየኢሬቻ በዓልን ለመረበሽ የተዘጋጁ 503 ሰዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ።