
በአማራ ክልል በፌዴራል መንግሥት ከሚገነቡት ፕሮጀክቶች መካከል የርብ መስኖ ግድብ ፕሮጀክት ከፍተኛ ችግር ያለበት፣ የግንባታ ሂደቱ በውስብስብ ችግሮች የተጓተተ ግዙፍ ፕሮጀክት ሆኗል፡፡ በዚህም አርሶ አደሮችን ይጠቅማል ተብሎ የተጀመረው ፕሮጀክት የችግራቸው ምንጭ ሆኗል፡፡
መንግሥትንም በየዓመቱ ለከፍተኛ ወጪ እየዳረገው ነው፡፡ ከሰሞኑ በፌዴራል መስኖ ኮሚሽን የኢትዮ-ናይል (ርብና መገጭ መስኖ) ፕሮጀክቶች አስተባባሪ ብርሃኑ አያሌው ለመዘግየቱ ምክንያቶችን ለመገምገም በሥፍራው የመስክ ምልከታ አድርገዋል፡፡ ምልከታው ችግሮችን በመለየት አፋጣኝ መፈፍሔ ለመስጠት ያለመ መሆኑንም ለአብመድ ተናግረዋል፡፡ መሬት ከሦስተኛ ወገን ነጻ አለመደረጉ ዋነኛው ችግር መሆኑንም አንስተዋል፡፡ የካሳ ግምት በትክክል እና በፍጥነት አለመሥራት፣ ለሕዝብ ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ አለመስጠት፣ የተወራረደ ካሳን ማዘግየት በክልል እና በወረዳዎች የታዩ ችግሮች መሆናቸው ተነስተዋል፡፡ በምልከታቸው በቂ ድጋፍ እና ክትትል እንደማይደረግ መረዳታቸውንም ተናግረዋል፡፡
ለቀረበ የካሳ ጥያቄ ተገቢ ምላሽ መሰጠቱን እና ያልተከፈለ ካለም በፍጥነት እንደሚስተካከልም ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን ለኮሚሽኑ ያልደረሱ የካሳ ጥያቄዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ አቶ ብርሃኑ አመላክተዋል፡፡ እነዚህ ጥያቄዎች ለግንባታው መጓተት መሠረታዊ ምክንያት እንደሚሆኑም ጠቅሰዋል፡፡ እንደ አስተባባሪው ገለጻ ችግሮችን ቶሎ በመፍታት ፕሮጀክቱ እንዲጠናቀቅ እየተሠራ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡
በተያዘው በጀት ዓመት ፕሮጀክቱን ለማጠናቀቅ ከሁሉም አካላት ጋር ውይይት መደረጉን ጠቅሰዋል፤ ኮሚሽኑ ሥራውን በአግባቡ እንዲፈጽም ክልሉ ድርሻውን ወስዶ ችግሮችን እንዲፈታ ጠይቀዋል፡፡
አቶ ብርሃኑ ይህን ይበሉ እንጅ የመሬት አቅርቦት ለመዘግየቱ መሠረታዊ ምክንያት እንዳልሆነ የአማራ ክልል የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ቢሮ አስታውቋል፡፡
ፕሮጀክቱን በባለቤትነት የሚያስተባብሩት የቢሮው ምክትል ኃላፊ መለሰ ዳምጤ እንዳሉት ክልሉ መሬት በ2006 እና በ2007 ዓ.ም ነው ከሦስተኛ ወገን ነፃ አድርጎ ያስረከበው፡፡ አርሶ አደሮችም ‹ይከፈለኛል› በማለት ካሳ ሳይከፈላቸው መልቀቃቸውን ጠቅሰዋል፡፡ በአንጻሩ ግን የካሳ ክፍያው ከ6 ወራት እስከ 2 ዓመታት እንደዘገየባቸው አንስተዋል፡፡ በዚህ መልኩ መሬት ነጻ ቢደረግም ቶሎ ወደ ሥራ አልተገባም፤ በግንባታ ተቋራጭ በኩል የጊዜ ማራዘሚያ እንደሚጠየቅም አንስተዋል፡፡
‹‹የግንባታ ተቋራጭ ዓመቱን ሙሉ ያለ ሥራ ቆይቶ ክረምት ሲገባ መሬት መቆፈር ይጀምራል›› በማለት የፕሮጀክት አስተዳደር ሥርዓቱ ደካማ መሆኑናን አግባብነት በጎደለው መልኩ ለተቋራጭ እና ለአማካሪ ድርጅት መሰጠቱ ክልሉን ከፍተኛ ዋጋ እንዳስከፈለው አንስተዋል፡፡ ኮሚሽኑም በአማካሪ ድርጅቱ እና በግንባታ ተቋራጩ ላይ የወሰደው ርምጃ እንደሌለም ጠቅሰዋል፡፡ ጉዳዩን የክልሉ ‘ስትሪንግ ኮሚቴ’ እና የተወካዮች ምክር ቤት በተደጋጋሚ የሚጨቃጨቁበት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
‹‹እንደ ርብ እና ሰራባ የመስኖ ፕሮጀክቶች በዚች ሀገር አላስፈላጊ ወጪ ያስወጣ ፕሮጀክት የለም፡፡ ችግሩም የኮንትራክተሮች እና የአማካሪ ድርጅቶች አላግባብ የመጠቀም እንቅስቃሴ ውጤት ነው፡፡ እኔ በግሌ በ2013 በጀት ዓመትም ግንባታው ይጠናቀቃል ብዬ አላምንም፡፡ አካባቢው ምንም ልማት ሳይሠራበት በጎርፍ እየተጥለቀለቀ፣ ሕዝብ አቤቱታ እያነሳ እንዲኖር የተፈለገበት አሻጥር ያለ ይመስለኛል›› በማለትም ችግሩ ከክልሉ መንግሥት አቅም በላይ እንደሆነ አንስተዋል፡፡
ከሰሞኑ አስተባባሪው ከስፍራው ‹አገኘሁ› ያሉትን ችግር ከቢሮው ጋር ሳይወያዩበት መመለሳቸው አግባብ እንዳልሆነም ገልጸዋል፡፡ ከበፊቱም አመረቂ ውይይት አለመደረጉን እና እምብዛም ውጤት እንዳልታየበት አንስተዋል፡፡ ያም ሆኖ ቀጣይ ችግሮችን ገጽ ለገጽ መወያየት እንደሚያስፈልግ አንስተዋል፡፡
በመርህ ደረጃ የመሬት ሽግሽግ የሚሠራው መሠረተ ልማት ከተጠናቀቀ በኋላ ቢሆንም ግንባታው ሳይጠናቀቅ ሽግሽግ እንዲሠራ ኮሚሽኑ መመሪያ ሰጥቷል፡፡ በ2010 ዓ.ም የመሬት ሽግሽግ መሠራቱንም አቶ መለሰ ተናግረዋል፡፡ አርሶ አደሩ መስኖ አልማ ተብሎ በሽግሽግ መሬት ከተሰጠው ሦስት ዓመታት አልፈውታል፡፡ ከሽግሽግ ቀጥሎ ልማት መጀመር ቢኖርበትም ነገር ግን የመስኖ ፕሮጀክቶቹ ሥራ ባለመጀመራቸው የልማት ሥራ መጀመር አልተቸቻለም፡፡
የመስኖ መሬት ሽግሽግ ምንድን ነው?
ሽግሽግ ወይም የመስኖ የመሬት ሥሪት ለግድብ ሥራ፣ ለውኃ ማከፋፈያ ዋና፣ አንደኛ ሁለተኛ፣ ሦስተኛ እና አራተኛ ቦዮች ከያንዳንዱ አርሶ አደሮች መሬት ይወሰዳል፡፡ ለዚህ መሠረተ ልማት የዋለውን መሬት ለተጠቃሚ አርሶ አደሮች ምን ያህል ድርሻ እንደሚሆን ስሌት ተሠረቶ አዲስ የመሬት ድልድል ሥራ ይከናወናል፡፡ ሁሉም መሬት የመረጃ ቋት ውስጥ ከገባ በኋላ በግንባታው መሠረት ይዞታው ሙሉ በሙሉ የሚነጠቅ አርሶ አደርም ተካትቶ በቀመሩ መሠረት ቅናሹ ተሰልቶ እንደገና ይደርሰዋል፡፡
አብመድ በርብ እና ሰራባ መስኖ ግድብ ፕሮጀክቶች ላይ የተስተዋሉ ችግሮችን የተመለከተ ዘገባ በተደጋጋሚ ሠርቷል፤ የፕሮጀክቶቹን አፈጻጸም መጓተት በተመለከተም በየጊዜው ጠይቋል፡፡ የሚሰጡት ምላሾች ግን ተተግብረው ውጤት ሲመጣ አልታዬም።
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ