የበረሃ አንበጣ መንጋውን ለመከላከል በአውሮፕላን የታገዘ የኬሚካል ርጭት እንዲደረግ አርሶ አደሮች ጠየቁ፡፡

370

ባሕር ዳር፡ መስከረም 21/2013ዓ.ም (አብመድ) በሰሜን ወሎ ዞን ራያ ቆቦ እና በሃብሩ ወረዳዎች የበረሃ አንበጣ መንጋ ወረርሽኝ በመስከረም መጀመሪያ ላይ ተከስቷል፤ ወረርሽኙን በአውሮፕላን የኬሚካልይ ርጭት መከላከል ካልተቻለ ከፍተኛ ውድመት ሊያደርስ እንደሚችል አርሶ አደሮች ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡

በምሥራቅ አማራ 55 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የበረሃ አንበጣ መንጋ ወረርሽኝ መከሰቱን የክልሉ ግብርና ቢሮ አሳውቋል፡፡ በሰሜን ወሎ ራያ ቆቦና ሀብሩ ወረዳዎችም ወረርሽኙ ከመከሰትም በላይ በሰብል ላይ ጉዳት ማድረስ መጀመሩን አርሶ አደሮች ተናግረዋል፡፡

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አጀበ ስንሻውና የዞኑ ግብርና መምሪያ ኃላፊ ዲያቆን ተስፋሁን ባታብል በራያ ቆቦ ወረዳ በመገኘት የወረርሽኙን የጉዳቱን ሁኔታ ጎብኝተዋል፡፡

አቶ አበጀ ለአብመድ በሰጡት ቃለ ምልልስ የበረሃ አንበጣ መንጋው በሰባት ወረዳዎችና 43 ቀበሌዎች ላይ መከሰቱን ገልጸዋል፤ አብዛኞቹ ሰብሎች በእሸት ደረጃ ያሉ በመሆኑ አደጋውን የከፋ እንደሚያደርገው ጠቁመው ከአጎራባች ክልሎች ጋር በመተባበር መሥራት እንደሚያስፈልግ አስታውቀዋል፡፡

የበረሃ አንበጣ መንጋ ወረርሽኙ ጉዳት መጀመሩን ያረጋገጡት የሰሜን ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ ዲያቆን ተስፋሁን ባታብል ግብርና ከአርሶ አደሮች ጋር በመተባበር በባህላዊ መንገድና በኬሚካል ርጭት ለመከላከል ጥረት እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በራያ ቆቦ ወረዳ የፎኪሳ ቀበሌ አርሶ አደሮች በሰጡን አስተያዬት ወረርሽኙ ከተከሰተ ጊዜ ጀምሮ የመከላከሉን ሥራ የሠሩ ቢሆንም አንበጣው መብረርና ወደሰብል ማሳ መግባት በመጀመሩን አስታውቀዋል፤ የከፋ ጉዳት ከማድረሱ በፊት መንግሥት በአውሮፕላን የታገዘ የኬሚካል ርጭት እንዲያደርግም ጠይቀዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ዋሴ ባየ -ከወልድያ

Previous articleዳሽን ባንክ ለገበታ ለአገር ፕሮጀክት የ30 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ።
Next articleበባለፈው የኢትዮ-ቴሌኮም የሪፎርም ሐሳቦች ዙሪያ ውይይት እየተደረገ ነው።