
ባሕር ዳር፡ መስከረም 21/2013ዓ.ም ባባለፈው ጳጉሜን 2/2012 ዓ.ም ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ (ዶከተር) በኢትዮ ቴሌኮም የሪፎርም ሥራ ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡ በቴሌኮምና በቴክኖሎጅ ዘርፍ ከተሰማሩ ኩባንያዎች ጋር በቴሌኮም ሪፎርም ዙሪያ ያላቸውን ሐሳብ እና የአሠራር ግብዓት እንዲያቀርቡ አቅጣጫ አስቀምጠው ነበር።
በተሰጠው አቅጣጫ መሠረትም የዘርፉ ባለሙያዎች፣ ባለድርሻ አካላት፣ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የውጭ ሀገራት ኩባንያዎች በተገኙበት በሸራተን አዲስ ውይይት እየተካሄደ ነው።
ኢትዮ-ቴሌኮም መንግሥታዊ እና የተቋማዊ ቁመናን ይዞ ለሕዝብ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ በርካታ አስርት ዓመታትን ተሻግሯል፤ አሠራሩን ለማዘመን እና አገልግሎት አሰጣጡን ቀልጣፋና በቴክኖሎጅ የተደገፈ ለማድረግ በተለይ ባለፉት ሁለት ዓመታት ተቋሙ ሪፎርም ውስጥ መግባቱ ተገልጿል፡፡ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ ኢትዮ-ቴሌኮምን ሪፎርም የማድረግና ተወዳዳሪ እና ተመራጭ የቴሌኮም አገልግሎት ሰጭ ለማድረግ የሦስት ዓመታት ስትራቴጅክ እቅድ ተቀርጾ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል፤ ለዚህ ደግሞ የአይ ቲ እና የቴክኖሎጅ ኩባንያዎች ሚና የጎላ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በዛሬው ዕለትም የኢትዮ-ቴሌኮም ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የፕራይቬታይዜሽን አማካሪዎች፣ 210 የሚደርሱ የአይ ሲ ቲ እና ቴክኖሎጅ ኩባንያዎች እየተሳተፉ ነው።
የውይይቱ ተሳታፊዎች ኢትዮ ቴሌኮም በሪፎርም ሥራው ማካተት እና መሥራት ያለበትን ምክረ ሐሳቦች አቅርበዋል።
ተቋሙ ተወዳዳሪ እና በቴክኖሎጅ የታገዘ አሠራርን መዘርጋት እንዳለበት፤ ለዚህ ደግሞ ገበያውን ለግል ባለሙያዎች ክፍት ማድረግ እንደሚገባ ተነስቷል፡፡ ኢትዮ ቴሌኮም ባለፉት ሰባት ወራት ጥሩ የሚባል ሥራ እየሠራ መሆኑ ጥሩ ጅምር እንደሆነ ተገልጾ ከ78 ዓመታት በላይ የሆናቸው የቴሌ ምሰሶዎች እና ሌሎች መሠረተ ልማቶች የቀጣይ 10 ዓመታትን ታሳቢ ያደረጉ ሆነው መዘርጋ እንዳለባቸው ተጠቁሟል፡፡
የተወሰነ ጊዜ የኢንተርኔት ድጎማ ጭምር በማድረግ የደንበኞችን ቁጥር ማሳደግ፣ ግልጽ የሆነ አሠራር መዘርጋት፣ የምንዛሪ እጥረትን ለመፍታት ዘርፉን በልዩ ሁኔታ መደገፍ እንደሚገባም ተጠቅሷል፡፡ ለሪፎርሙ በቂ ጊዜ ያስፈልጋል፣ የኢትዮ-ቴሌኮም ደንበኞች አሁን ከድምጽ ወደ ዳታ እየዞሩ በመሆኑ እና ከግሉ የቴክኖሎጅ እና የአይ ቲ ባለሙያዎች ጋር ብዙ መሥራት እንደሚጠበቅም ሐሳብ ተሰጥቷል፡፡
ከውጭ አቅም ያላቸው ኩባንያዎች ሲገቡ ሀገር ውስጥ ያሉትንም የሚያሳትፍ አሠራር መኖር እንዳለበት፤ ኩባንያዎቹ ተደራሽነት በሀገር አቀፍ ደረጃ እንዲሆን መሥራት እንደሚገባም ተጠቁሟል፡፡
የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ አሁን ያለው የዘርፉ ፍላጎት እያደገ መምጣቱንና አገልግሎቱን ተደራሽ እና ጥራት ያለው ለማድረግ ባለድርሻ አካላቱን ያሳተፈ ሥራ ለመሥራት በሩ ክፍት መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡
አሁን 7 ሺህ 123 የሞባይል (ታወሮች) መኖራቸውን እና በዘርፉ የሚሰማሩት ደግሞ የራሳቸውን መሠረተ ልማት ቢዘረጉ ይበልጥ አገልግሎቱን ማሳደግ እንደሚቻልም ጠቁመዋል፡፡ ነገር ግን አሁን ያሉትን ታወሮች በማከራየት አቅምንም ማሳደግ እንደሚቻል አስረድተዋል።
በዘርፉ ለመሰማራት ከውጭ ለሚመጡ ሁለት ኩባንያዎች ለዘርፉ አዳዲስ ቴክኖሎጂ ከማምጣት ባሻገር ከፍተኛውን የውጭ ምንዛሬ ማለትም ከ1 ነጥብ 6 እስከ 1 ነጥብ 8 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ይዘው እንዲገቡ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑንም ወይዘሪት ፍሬሕይወት ታምሩ አስታውቀዋል፡፡
“የኛ ኢትዮ ቴሌኮም ዘርፍ ትልቅ መሠረተ ልማት የዘረጋ ነው፤ ለዚህ ደግሞ ጥቅም ማግኘት አለበት፤ አዳዲስ የሚለሙ ከተሞችን ተደራሽ ለማድረግም ከወዲሁ እየተሠራ ነው” ብለዋል ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ፡፡ የፋይናንስ አቅምን ለማመቻቸት ከብሔራዊ ባንክ ጋር መነጋገር መጀመራቸውንም ጠቅሰዋል።
ዘርፉን ለማሻሻል የዘርፉ ኩባንያዎች የሥራ እቅድ ማስገባት እንዳለባቸው የጠቆሙት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ “በጋራ ከሠራን ለውጡን በመተጋገዝ ወደፊት ይዞ መውጣት ይቻላል” ብለዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ሁሉንም እገዛ እንደሚያደርጉም ቃል ገብተዋል፡፡ የቴሌኮም ማጭበርበርን ለመፍታት እርምጃዎች መጀመራቸውንና ባለፈው ዓመት በተሠራው ሥራ 147 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱንም አንስተዋል፡፡ በዘርፉ ከሚሰማሩት ጋር የሀገርን ጥቅም ባስቀደመ መልኩ እንደሚሠራም ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፦ ጋሻው ፈንታሁን- ከአዲስ አበባ