ዳሽን ባንክ ለገበታ ለአገር ፕሮጀክት የ30 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ።

244

ዳሽን ባንክ ለገበታ ለአገር ፕሮጀክት ግንባታ የ30 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርጓል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ገበታ ለአገርን ባስጀመሩበት ወቅት “ገንዘብ፣ ዕውቀት እና ጉልበት በማሰባሰብ ተፈጥሮን ሳናውክ ለዜጎችም ለውጭ ቱሪስቶችም የምትመች ኢትዮጵያን እንፈጥራለን” ማለታቸው ይታወሳል።

ነሐሴ 10 ቀን 2012 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትሩ ይፋ በተደረገው መርሐ ግብር 3 ቢሊዮን ብር ወይም 100 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ለማሰባሰብ ያለመ ነው፡፡

ለሦስቱ ፕሮጀክቶች ግንባታ 2 ቢሊዮን ብር ይመደባል ማለታቸውንም የኢዜአ ዘገባ አስታውሷል፡፡

በዚህም ዳሽን ባንክ ዛሬ ይፋ ባደረገው ድጋፍ መሠረት ለእያንዳንዱ ፕሮጀክት ግንባታ የ10 ሚሊዮን በድምሩ 30 ሚሊዮን ብር ለግሷል።

የቦታ ማስዋብና የተለያዩ መሠረተ ልማት ግንባታዎች እንዲከናወንላቸው የተመረጡት ሦስት ሥፍራዎች በአማራ፣ በኦሮሚያና በደቡብ ክልሎች ይገኛሉ፡፡

በአማራ ክልል የሚለማው ሥፍራ ጎርጎራ ሲሆን ጣና ሐይቅ አካባቢ የሚገኝና ጎንደርና ባሕር ዳር ከተሞች የሚጋሩት በተፈጥሮ ሀብት የታደለ አካባቢ ነው፡፡

በኦሮሚያ ክልል የሚገኘው ደግሞ ለምለም የሆነው የወንጪ ሐይቅ ነው፡፡

ከደቡብ ክልል የተመረጠው ሥፍራም ኮይሻ የሚባል ቦታ ሲሆን በዳውሮ፣ ወላይታ፣ ጊቤ ሦስትና በኮንታ መካከል የሚገኝና የጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክ መገኛ ሥፍራ ነው፡፡

ገበታ ለአገር ፕሮጀክት የሚዋጣው የገንዘብ መጠን ቪ.ቪ.አይ.ፒ 10 ሚሊዮን ብር እንዲሁም ቪ.አይ.ፒ 5 ሚሊዮን ብር ያስከፍላሉ፡፡

የግሉ ዘርፍ ባለሀብቶች፣ ኩባንያዎች፣ ዳያስፖራው፣ እንዲሁም የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ ለእነዚህ ፕሮጀክቶች አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉም ይጠበቃል።

የገንዘቡ ገቢ በባንክ አካውንት ቁጥር የሚጠራቀም ሲሆን በተያዘው የመስከረም መጨረሻ አልያም ጥቅምት አጋማሽ አካባቢ የታለመለት የእራት መርሐ ግብር እንደሚከናወን ይጠበቃል፡፡

Previous articleየበረሃ አንበጣ መንጋን የመከላከል ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
Next articleየበረሃ አንበጣ መንጋውን ለመከላከል በአውሮፕላን የታገዘ የኬሚካል ርጭት እንዲደረግ አርሶ አደሮች ጠየቁ፡፡