የበረሃ አንበጣ መንጋን የመከላከል ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

360

በአሁኑ ወቅት የበረሃ አንበጣ መንጋዉ በኢትዮጵያ በአፋር ክልል በ26 ወረዳዎችና በምሥራቅ አማራ አጎራባች ወረዳዎች እና በሱማሌ ክልል በሲቲ ዞን በሚገኙ በአይሻ፣ አወበሬ እና ሽንሌ ወረዳዎች በሀገር ውስጥ የተጣሉ የበረሃ አንበጣ እንቁላል በመፈልፈሉና ከሶማሊ ላንድ በመግባት ዳግም ተከስቷል።

የበረሃ አንበጣ መንጋው በግጦሽና ሰብል ላይ ጉዳት እንዳያደርስ በሁለት የቅኝት ሄሎኮፕተሮችና በአራት የኬሚካል መርጫ አዉሮፕላኖች እንዲሁም መኪና ላይ በሚገጠሙና በሰዉ ጉልበት በሚሠሩ የመርጫ መሣርያዎች የታገዘ የመከላከልና የመቆጣጠር ሥራ በአየርና በምድር ተጠናክሮ መቀጠሉን የግብርና ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

ሚኒስቴሩ እንዳለው የበረሃ አንበጣ መንጋ ወረርሽኙ እስካሁን በሰብል ላይ ጉዳት ባያደርስም በግጦሽ ሳርና በቁጥቋጦ ላይ ጉዳት እያስከተለ ይገኛል፡፡ በዚሁ መሠረት በአፋር እና ሶማሌ ክልሎች የተከሰተዉ የበረሃ አንበጣ ባለበት ለመቆጣጠርና ወደ አማራ፣ ኦሮሚያ እና ትግራይ ክልሎች በመዛመት ሰብል ላይ ጉዳት እንዳያደርስ የግብርና ሚኒስቴር ከክልሎች ጋር ጠንካራ አደረጃጀት በመፍጠር እና አስፈላጊዉን የኬሚካል፣ የተሽከርካሪዎች፣ የአሰሳ ሄሊኮፕተሮችና የመርጫ አውሮፕላኖች እንዲሁም በቂ ባለሙያዎችን በመመደብ ከዓለም አቀፍ አጋር አካላት ጋር ቅንጅት በመፍጠር የመቆጣጠር ሥራ እየሠራ ይገኛል፡፡

የበረሃ አንበጣ መንጋው በኢትዮጵያ ከሰኔ 2011ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ ክልሎች ቆላማ ቦታዎች የተከሰተ ሲሆን የመከላከል ሥራዉ በቀጣይነት ሲሰራ ቆይቷል፡፡ ሚኒስቴሩ እንዳስታወቀው ከሰኔ 2011 ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ በሰባት ክልሎችና በአንድ ከተማ አስተዳደር (አፋር፣ ሶማሌ፣ አማራ፣ ትግራይ፣ ደቡብ፣ ኦሮሚያ፣ ሐረሪ እና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር) በ178 ወረዳዎቸ ተከስቷል፡፡ የበረሃ አንበጣ መንጋዉ ከየመን፣ ሶማሌላንድ፣ ሶማሊያ እና ኬኒያ በመነሳት በተለያዩ ጊዜያት ወደ ኢትዮጵያ ሲገባ የነበረ መሆኑንና በኢትዮጵያ ዉስጥም መንጋዉ የጣለዉ እንቁላል በተለያዩ ቆላማ ቦታዎች የተፈለፈለበት ሁኔታ መኖሩንም ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡

የበረሃ አንበጣ ጉዳት እንዳያደርስ ግብርና ሚኒስቴር ከክልሎች እና ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር ጠንካራ ቅንጅት በመፍጠር እና አስፈላጊ ግብዓቶችን በማሟላት ሕዝቡን ባሳተፈ መልኩ የመከላከል ሥራ ሲሠራ መቆየቱን አመልክቷል። የመከላከል ሥራዉ ተጠናክሮ መቀጠሉም ታውቋል፡፡

የበረሃ አንበጣ መንጋዉን ለመከላከል በተደረገው ሁለገብ እንቅስቃሴ ከሰኔ 2011 ዓ.ም ጀምሮ በ1 ሚሊዮን 307 ሺህ 306 ሄክታር መሬት ላይ አሰሳ ተካሂዶ 528 ሺህ 880 ሄክታር መሬት ላይ መከሰቱን አረጋግጧል፤ 468 ሺህ 827 ነጥብ 45 ሄክታር የግጦሽና የእርሻ መሬት ላይ የፀረ-ተባይ ኬሚካል ርጭት በማካሄድ እና የተቀረዉን ሕዝቡን በማሳተፍ በባህላዊ ዘዴ ጉዳት እንዳያደርስ የመከላከል ሥራ መሠራቱም ተመላክቷል፡፡

በ2011/12ዓ.ም ምርት ላይ ያደረሰዉ ጉዳት በተመለከተ በተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በተደረገዉ ግምገማ መሠረት የበረሃ አንበጣ መንጋ 3. ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል (ከዓመቱ ምርት ውስጥ አንድ በመቶ የሚሆን) ምርት ጉዳት ማድረሱን በተደረገው ጥናት መለየቱ ይታወሳል፡፡

በዘንድሮው የቁጥጥርና የመከላከል ሥራም በግጦሽ፣ በቁጥቋጦና በሰብል ላይ የሚደርሰውን የጉዳት መጠን ለመቀነስ የተቀነጀ ርብርብ ማድረግ እንደሚጠበቅ ሚኒስቴሩ አሳስቧል፡፡ እስካሁን በተሠራዉ ሥራ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ከክልሎች ጋር በመቀናጀት እና ሕዝቡን በማሳተፍ በተሠራዉ ሥራ ጥሩ ዉጤት እየተመዘገበ ያለ ሲሆን የመከላከሉና የመቆጣጠሩ ሥራ የበለጠ ውጤታማ ሊሆን የሚችለው የዞንና የወረዳ መዋቅር መላውን አርሶና አርብቶ አደሩን ኅብረተሰብ በባለቤትነት መንፈስ በማንቀሳቀስ ከግብርና ሚኒስቴር እና አጋር አካላት የተገኘዉን ድጋፍ ዉጤታማ በሆነ መልኩ ሥራ ላይ እንዲውል ሲያደርግ ብቻ እንደሆነ እንደሚታመን ሚኒስቴሩ ገልጧል፡፡

ለዚህም በተዋረድ የሚገኙ የመንግሥት መዋቅሮች ኅብረተሰቡን በሚፈለገዉ ደረጃ በማሳተፍ እና ቅንጅታዊ አሠራርን በማጠናከር የተጀመረዉ የበረሃ አንበጣ መንጋ የመከላከልና የመቆጣጠር ሥራ ርብርብ በማጠናከር የበኩላቸውን እንዲወጡ የግብርና ሚኒስቴር ጥሪ አቅርቧል፡፡

Previous articleበንፁኃን ላይ የሚደርሰውን ጥቃት በዘላቂነት ለማስቆም ሕገ መንግሥቱንና የሕግ ተቋማትን ማሻሻል እንደሚገባ የሕግ ምሁር ተናገሩ።
Next articleዳሽን ባንክ ለገበታ ለአገር ፕሮጀክት የ30 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ።