በንፁኃን ላይ የሚደርሰውን ጥቃት በዘላቂነት ለማስቆም ሕገ መንግሥቱንና የሕግ ተቋማትን ማሻሻል እንደሚገባ የሕግ ምሁር ተናገሩ።

119

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚደርሰውን ጥቃት በዘላቂነት ለማስቆም የክልሉን ሕገ መንግሥት እና የሕግ ተቋማትን እንደገና መቃኘት እንደሚያስፈልግ የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህር ዓለምሰገድ ደጀኔ ገልጸዋል።

እንደ መምህሩ ማብራሪያ በኢትዮጵያ የፌዴራል ሕገ መንግሥቱን ጨምሮ የክልሎች ሕገ መንግሥታት ብዙ ክፍተቶች አሉባቸው። ከዘመኑ ጋር ለመዘመን ደግሞ የሕጎች ሁሉ የበላይ የሆነውን ሕገ መንግሥቱን ፈትሾ ማሻሻል ዓይነተኛ መፍትሔ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡ ከፌዴራል ሕገ መንግሥት የተቀዳው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሕገ መንግሥትም በክልሉ ውስጥ ለሚገኙ ለተወሰኑ ብሔረሰቦች ብቻ የባለቤትነትን መብት የሚያጎናፅፍ እና በርካቶችን ያገለለ እንደሆነ ጠቅሰዋል።

የሕግ መምህሩ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ብሔራዊ ክልል ሕገ መንግሥት አንቀጽ 2 ላይ ነባር ብሔረሰቦች ለሚላቸው ብቻ የክልሉ ባለቤቶች መሆናቸውን ማወጁን ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡ በሕብረ ብሔራዊት ሀገር ይህ አንቀጽ አደገኛ ስለሆነ ማሻሻያ እንደሚያስፈልገውም ጠቁመዋል።

ከሰሞኑ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በታጠቁ አካላት የንፁኃን ሕይወት ከማለፉ እና መፈናቀል ጋር ተያይዞ 45 የሥራ ኃላፊዎች ላይ እርምጃ መወሰዱ ተገቢ መሆኑንም ተናግረዋል። የሕግ መምህሩ ዘላቂ መፍትሔ ግን እንደማይሆን ነው ያስረዱት።

መፍትሔውም በሕገ መንግሥቱ የተቃኙትን የሕግ ተቋማት መፈተሽ፣ በክልሉ ውስጥ ለሚገኙት ሕዝቦች ሕጋዊ ውክልና መስጠት እና መንግሥት የዜጎችን ደኅንነት በዘላቂነት መጠበቅ እንደሆነ አመላክተዋል።

መንግሥት ግጭት ሲፈጠር፣ ዜጎች ሲፈናቀሉ እና የሰው ሕይወት ሲያልፍ እሳቱን ከማጥፋት ወጥቶ የቅድመ መከላከል ሥራዎችን መሥራት እንዳለበትም አብራርተዋል። “በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ያለው ችግር አሁን የተፈጠረ አይደለም” ያሉት የሕግ መምህሩ ጥቃት አደረሱ የተባሉት ታጣቂዎች ብሔርን መሠረት አድርገው ጥቃት መፈፀማቸው ለሌሎቹ ብሔሮች ዕውቅና ካለመስጠት የመነጨ እንደሆነ ገልጸዋል። መንግሥት ዜጎች በተረጋጋ አካባቢ እንዲኖሩና ጥበቃ ማድረግ፣ ጥቃት የሚያደርሱ አካላትን በሕግ ተጠያቂ ማድረግ እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡

ዘጋቢ:- አዳሙ ሽባባው

Previous articleአፍሪካ በሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር ምክንያት በየዓመቱ በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ታጣለች፡፡
Next articleየበረሃ አንበጣ መንጋን የመከላከል ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡