አፍሪካ በሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር ምክንያት በየዓመቱ በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ታጣለች፡፡

233

ባሕር ዳር፡ መስከረም 21/213ዓ.ም (አብመድ) አፍሪካ እንደግብር ማጭበርበር፣ የሮያሊቲ ክፍያ መደበቅና መሰል ሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር በየዓመቱ 89 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገደማ ገንዘብ እንደምታጣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጥናት አመላከተ፡፡

በሕገ-ወጥ መንገድ የምታጣው ገንዘብ ለልማት ሥራዎች በዕርዳታ ከምታገኘው የበለጠም ነው ተብሏል፡፡

ባለፈው ሰኞ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የንግድ እና ልማት ምክክር ላይ አህጉሪቷን “ትርፍ አልባ አበዳሪ” የሚል መጠሪያ ሰጥቷታል፡፡

አፍሪካ ወደውጭ ከምትልካቸው እንደ ወርቅ፣ አልማዝ እና ፕላቲኒየም የምታጣው ገንዘብ ከጠቅላላው ግማሽ ያክሉን ይሸፍናል ነው የተባለ፡፡ ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን ክፍያ እና ግብር የሚወስኑ ተቋማት እንደሚያጭበረብሩም ነው በሪፖርቱ የተገለጸው፡፡ የሸቀጦችን እውነተኛ እሴት የመረዳት ችግር ግብር እና የውጭ ምንዛሪ እንዲያጡ ምክንያት መሆኑም ተጠቁሟል፡፡

አህጉሪቷ በውጭ ዕርዳታ ላይ ጥገኛ ብትሆንም በግብር ማጭበርበር እና በሕገ-ወጥ መንገድ የምታጣው ገንዘብ ትርፍ አልባ አበዳሪ እንዳደረጋት ነው የዘርፉ ምሁራን የሚጠቁሙት፡፡

በየዓመቱ የምታጣው ገንዘብ ለጤና መሠረተ ልማት እና እንደኮሮናቫይረስ ያለ ችግር በተከሰተ ጊዜ ከሥራ ለሚቀነሱ ዜጎቿ ማኀበራዊ ዋስትና መሆን ይችል ነበር፡፡ የአህጉሪቱ የማኅበረሰብ አንቂዎች አህጉሪቷ ጠንካራ የሕግ ማዕቀፍ እና አሠራር ልትዘረጋ እንደሚገባም እየሞገቱ ነው፡፡

ምንጭ፡- አፍሪካ ኒውስ

በታዘብ አራጋው

Previous articleአምስት የጥረት ኮርፖሬት ኩባንያዎች ታማኝ ግብር ከፋዮች ሆነው ተሸልመዋል።
Next articleበንፁኃን ላይ የሚደርሰውን ጥቃት በዘላቂነት ለማስቆም ሕገ መንግሥቱንና የሕግ ተቋማትን ማሻሻል እንደሚገባ የሕግ ምሁር ተናገሩ።