
ባሕር ዳር፡ መስከረም 21/213ዓ.ም (አብመድ) በታማኝ ግብር ከፋይ ከተሸለሙት ስምንት በአማራ ክልል የሚገኙ ድርጅቶች ዉስጥ አምስቱ የጥረት ኮርፖሬት ናቸው። አምባሰል ንግድ ሥራዎች፣ ኮምቦልቻ ጨርቃጨርቅ፣ ቢዲሲ ኮንስትራክሽን፣ ዳሸን ቢራ እና ተክራርዋ የፕላስቲክ ውጤቶች ማምረቻ ተጠቃሽ ናቸው።
አምባሰል የንግድ ሥራዎች በግብርና ምርት በቅባት እህሎች የደን ዉጤቶች ያመርታል፤ በሁለተኛ ደረጃ የወርቅ ተሸላሚ ነው። ባለፉት ሦስት ዓመታት 82 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ አስገብቷል። ባለፉት ሦስት ዓመታት 171 ሚሊዮን ብር ለመንግሥት ገቢ አድረጓል፤ ይህም በዓመት አማካኝ ከ50-60 ሚሊዮን ማለት ነው።
የኮምቦልቻ ጨርቃ ጨርቅ አክሲዮን ማኅበር በዓመቱ በሀገር ዉስጥ ገበያ 322 ሚሊዮን ብር ሸጧል፤ 19 ሚሊዮን በላይ ከኤክስፖርት አግኝቷል የታማኝ ግብር ከፋይነትም ተሸልሟል።
ቢዲሲ ኮንስትራክስን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የብር ደረጃ ተሸላሚ ነው። ባለፉት አምስት ዓመታት ፋብሪካዎችን፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ ሆስፒታሎች ጨምሮ ሌሎች ግንባታዎችን አከናዉኗል።
ዳሸን ቢራ አክስዮን ማኅበር ባለፉት 20 ዓመታት ከፍተኛ ግብር ከፋይ ነዉ። የ2012ዓ.ም ከፍተኛ ግብር ከፋይ በመሆን የወርቅ ተሸላሚ ሆኗል።
ተክራርዋ የፕላስቲክ ዉጤቶች ማምረቻ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር በሁሉም የታክስ ዓይነቶች ያበረከተው የገቢ አስተዋጽኦ በበጀት ዓመቱ ከፍተኛ በመሆኑ ለሽልማት በቅቷል።
በገቢዎች ሚንስቴር በተዘጋጀው የ2012 በጀት ዓመት ታማኝ ግብር ከፋይ ሽልማት ከተመረጡ 200 የንግድ ተቋማት አንዱ በመሆን የብር ተሸላሚ ሆኗል። በዚህ ወቅት ኩባንያው ካፒታሉን ከ110 ሚሊዮን በላይ ብር በማድረስ ተጨማሪ ምርቶች ለኅብረተሰቡ ለማድረስ እየሠራሁ ነዉ ብሏል።
ዘጋቢ፦ ጽዮን አበበ -ከአዲስ አበባ