ሁለት የኢትዮጵያ ሚንስትሮች ከሰሞኑ ዓለማቀፍ ሽልማት አሸንፈዋል።

126

ባሕር ዳር፡ መስከረም 21/213ዓ.ም (አብመድ) የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል እና የገንዘብ ሚንስትር አህመድ ሺዴ ከሰሞኑ ሽልማቶችን አሸንፈዋል።

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ የ2020 የአፍሪካ ቢዝነስ ሥራ አመራር ሽልማትን ነው የተቀበሉት።

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል የ2020 የአፍሪካ ቢዝነስ ሥራ አመራር ሽልማት አሸናፊ ሆነዋል።

አቶ መላኩ ለዚህ የላቀ ሽልማት የበቁት የንግድና ኢንዱስትሪ አጠቃላይ መዋቅሩን ከፌዴራል እስከ ክልልና ከተማ አስተዳደር ድረስ በማነቃነቅ በሀገር ደረጃ የተረጋጋ የግብይት ሥርዓት እንዲፈጠር በመሥራታቸው መሆኑን ሚኒስቴሩ አስታውቋል።

ሚኒስቴሩ አያይዞም ለኮሮናቫይረስ ተፅዕኖ የማይበገርና የሰከነ ንግድና ኢኮኖሚ እንዲኖር፣ የሀገር ውስጥ ንግድ እንዲያንሰራራ፣ ሀገራዊ የኤክስፖርት ንግድ እንዲነቃቃ በማድረጋቸው መሆኑንም አመልክቷል።

አቶ መላኩ አምራች ኢንዱስትሪዎች የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መከላከያ ግብዓቶችን እንዲያመርቱ በማድረግ አርአያነት ያለውን አመራር በመስጠታቸው መሆኑን ሚኒስቴሩ በፌስቡክ ገጹ ገልጿል።

ሽልማቱ የንግድና ኢንዱስትሪ ሴክተር አመራሮችና ሠራተኞች የጋራ ጥረት፣ የንግዱ ማኅበረሰብና የአምራች ኢንዱስትሪ ተዋናዮች ከፍተኛ ተሳትፎና ትብብር ውጤት መሆኑን ሚኒስቴሩ አመልክቷል።

የአፍሪካ ቢዝነስ ሥራ አመራር ሽልማት በተቋም፣ በሀገርና በአህጉር ደረጃ በቢዝነስ አመራር በላቀ ደረጃ ውጤታማ ለሆኑ ጥቂት መሪዎች የሚበረከት የመልካም ተግባር ዕውቅና ሽልማት እንደሆነ ኢዜአ ዘግቧል።

የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴም የዓመቱ ምርጥ የአፍሪካ ገንዘብ ሚኒስትር ሽልማትን ተቀብለዋል።

ሚኒስትሩ ሽልማቱን የተቀበሉት በ5ኛው የአሜሪካ-አፍሪካ ኢንቨስትመንት የፖሊሲ ውይይት መድረክ ላይ ነው።

ሽልማቱ እ.አ.አ በጥቅምት 2018 በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ የገንዘብ ሚኒስትር ሆነው እንዲያገለግሉ የተሰጣቸውን ኃላፊነት ለመወጣት ባሳዩት ቆራጥ የሥራ አመራርና በተለይም በኢትዮጵያ እየተካሄዱ ያሉ ጥልቅ የኢኮኖሚ ሪፎርሞችን በመምራት መሆኑ ተገልጧል።

በአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች በሳል አመራር በመስጠት፣ ከልማት አጋሮች የውጭ ሀብት ፍሰት እንዲጨምር በማደረግና የአገሪቷ የብድር አስተዳደር በአግባቡ እንዲመራ ማስቻላቸው አቶ አህመድ ሺዴን ለሽልማቱ ካበቋቸው መካከል ተጠቅሰዋል።

ከአበዳሪ አገራትና ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት የብድር መክፈያ ጊዜ እንዲራዘም በማድረግ የነበራቸው ጉልህ ድርሻም ግምት ውስጥ ገብቷል።

ኢትዮጵያ ከምሥራቅ አፍሪካ አገራት ጋር ያላት ኢኮኖሚያዊ ትብብር እንዲጠናከር ከፍተኛ ሚና እንደነበራቸውም በሽልማት ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ተገልጿል።

የገንዘብ ሚኒስትሩ በዓለምና በአገር አቀፍ ደረጃ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በተከሰተበት ጊዜ ጉዳቱን ለመቋቋም የሚያስችሉ የገንዘብና የፖሊሲ ውሳኔዎችን በማራመድ ከፍተኛ ተፅዕኖ ላደረባቸው የኢኮኖሚ ዘርፎች አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ ችለዋል ተብሏል።

እነዚህ ውሳኔዎች ወረርሽኙ ሊያስከትል የሚችለውን ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖ በመታደግ ወሳኝ አስተዋፅኦ እንደነበራቸውም ተጠቅሷል።
ሚኒስትሩ ሽልማቱን ከተቀበሉ በኋላ ባደረጉት ንግግር “2020 ለሁላችን አስቸጋሪ ዓመት ነበር፤ በዓለማችን ታይቶ የማይታወቅ ወረርሽኝ ተከስቶ በርካታ ተግዳሮቶች እንደፈጠረ በማስታወስ ሕይወት ለማዳን ብሎም ፈጣን ኢኮኖሚዊ ዕድገት ለማስቀጠል ትልቅ ፈተና ገጥሞናል” ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በዚህ ፈታኝ ወቅት ይህ ሽልማት መገኘቱ በኢትዮጵያ መንግሥት ተግዳሮቶቹን ለመወጣት ላደረገው ጥረት ዕውቅና እንደሚሰጥ አቶ አህመድ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ባለፉት አስርታት በመሠረተ ልማትና በሰው ሀብት ከፍተኛ መሻሻል የታየ ቢሆንም የግሉ ዘርፍ ሚና በሚፈለገው ደረጃ ላይ ባለመድረሱ ይህንን የልማት አጋር ለማጎልበት ወደ ዘላቂ የልማት ጎዳና የሚወስዱ ፕሮግራሞች እንደተቀየሱም ገልጸዋል።

“ይህ የጀመርነው መንገድ በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በድህነት ቅነሳና ሁሉን አቀፍ የዕድገት መንገድ ለማስቀጠል ያመቻቻል የሚል እምነት አለን” ብለዋል።

በአሜሪካ-አፍሪካ ኢንቨስትመንት ፎረም የፖሊሲ አውጪዎችን፣ የግሉ ሴክተር መሪዎችን፣ የኢንዱስትሪ አካላትን፣ ሲቪል ማኅበራትና በአሜሪካ-አፍሪካ የሚገኙ ባለድርሻ አካላትን በማሰባሰብና የወደፊት ግንኙነቶችን በሚያግዙ የፖሊሲ አቅጣጫዎች የልምድ ልውውጦች ተደርገዋል።

በመድረኩ ላይ የአሜሪካ-አፍሪካ ኢኮኖሚያዊ ትብብርና የኢንቨስትመንት ዕድሎች ላይ ምክክርም ተካሂዷል።

Previous articleየግሼን ደብረ ከርቤ የንግሥ በዓል እየተከበረ ነው።
Next articleበቀጣይ 10 ዓመታት የክልሉን ስፖርት ለማሳደግ የሚረዳ ግምገማ በባሕር ዳር እየተካሄደ ነው።